ተምሳሌት እናቶች በይፋ ሊሸለሙ ነው

53
ነሀሴ  9/2011 ብዕሲት ኢትዮጵያ ተምሳሌት እናቶችን በመሸለም እናት ክብርም ፤ የስኬትም መንገድ መሆኗን የሚያሳይ ዝግጅት ሊካሄድ ነው። የሽልማት ፕሮግራሙ "እናት ክብርም፣ የስኬትም መንገድ ናት" በሚል መሪ ሐሳብ ለእናቶች የሚገባቸውን ክብር ለመስጠትና ተምሳሌት የሆኑ እናቶችን በጎ ተሞክሮ እንዲያስተላልፉ ያለመ መሆኑ ተነግሯል። ሽልማቱ አስራ አምስት የተለያዩ ዘርፎችን የያዘ ሲሆን በእያንዳንዱ ዘርፍ መልካም ተጽእኖ ፈጣሪ እና ተምሳሌት የሆኑ እናቶች ከሁሉም ክልል ተመልምለው በሽልማቱ እንደሚካተቱ የሁነቱ አዘጋጅ አቶ ጌታቸው በለጠ ተናግረዋል። የዚህ ዓይነቱ ሽልማት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ይህ የተምሳሌት እናቶች የሽልማት ስነ-ስርዓት ህዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። ምርጫው በምን መንገድ ይካሄዳል የሚለውን ደግሞ በሚዲያዎች የታገዙ ተግባራት እንደሚኖሩት ተገልጿል። የፕሮግራሙ ባለቤትና አስተባባሪ 'ዮቤግ ኮሙኒኬሽን ሚዲያና ፐብሊሽንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር' ሲሆን ዳኞቹን በተመለከተም በአገሪቷ ካሉት በጎ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መካከል አምስት ሰዎች ተመርጠው በየዘርፎቹ ተሸላሚ እናቶችን እንዲለዩ እንደሚደረግም ታውቋል። በዝግጅቱም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እንደሚሳተፉበትና ፕሮግራሙ ከዚህ በኋላ በየአመቱ እንደሚቀጥልም ተገልጿል። ብዕሲት የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጓሚውም ሴት ማለት ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም