ኢትዮጵያና ቻይና በትብብር እንደሚሰሩ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አስታወቁ

72
ኢዜአ ነሃሴ 9/ 2011 በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከኢ ሲ ኤን ኤስ ድረ-ገፅ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁለቱ ሃገራት በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ በሚያካሂዱት የንግድ ትብብር ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ በማከልም ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች በማስፋት ያሏትን ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶች ዝግጁ የሆነ ገበያ እንደሚያገኙ እምነቴ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሂደቱ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችም ቢኖሩ እንኳን “የቻይና እገዛ እንደማይለየን እምነታችን የፀና ነው” ሲሉም አምባሳደሩ ተደምጠዋል፡፡ በሁለቱ ሃገራት የጋራ ትብብር በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የተገነባውን የአዲስ አበባ - ጂቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት አፈፃፀምን አምባሳደሩ አድንቀዋል፡፡ በቻይና የተገነባው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መንገድም ሰባት ቀናት ይወስድ የነበረውን መንገድ በአንድ ቀን በማሳጠር የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ሸቀጦችን በማጓጓዝ የማይተካ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም በዘገባው ተመልክቷል፡፡ የቻይና የኢንቨስትመንት ኢንተርፕራይዞች በተለይም በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ እንደሚገኙም በዘገባው ሰፍሯል፡፡ አምባሳደሩ በቃለ መጠይቃቸው ወቅትም የቻይና ኢንቨስትመንት ኢንተርፕራይዞች የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማፋጠን በተጨማሪ ህዝባችንንም በተጨባጭ ተጠቃሚ እያደረገ መጥቷል  ብለዋል፡፡ አምባሳደሩ በማከልም ቻይና በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ረገድ ባለፉት 40 ዓመታት ስላስመዘገበችው ውጤት እና ስላለው ትልቅ ለውጥ የተናገሩ ሲሆን የቻይናውያንን ትጋት የተሞላበት የስራ ባህልንም አድንቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም