በአርባምንጭ ከተማ 10 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል

58
አርባምንጭ ኢዜአ ነሀሴ 8 / 2011 ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ተጠቃሚ መሆናቸውን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። በአርባ ምንጭ ከተማ የሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት በከተማዋ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች በከተማዋ ተሰማርተዋል ብሏል ። በከተማዋ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሴ ከበደ በሰጡት አስተያየት ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ወጣቶቹ በሰላም እሴቶች ዙሪያ የሚሰጡት የህግ ግንዛቤ ትምህርት በገንዘብ የማይተመን ነው ብለዋል ፡፡ ሰላም በሌለበት ሰብአዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ሊረጋገጡ የማይችሉ በመሆናቸው ወጣቶቹ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀሳቸው የሚደነቅ ነው ብለዋል ። የድል ፋና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ደጉ በበኩላቸው በከተማዋ ከጽዳት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት የከተማዋ ወጣቶች በጽዳትና ውበት ስራ ተሰማርተው እያከናወኑት ያለውን ተግባር ከገንዘብ በላይ መሆኑን አስረድተዋል ። ከመንገድ ደህንነት ጋር በተያያዘ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ወጣቶቹ ህብረተሰቡን በመንገድ አጠቃቀምና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በማስተማር እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሶስተኛ ጊዜ እየተሳተፈ ያለው በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ተማሪ ታረቀኝ ቱኮ እንዳለው ሳይማር ያስተማረንን ማህበረሰብ ማገልገል ትልቅ እርካታን የሚሰጥ ተግባር ነው ብሏል ። ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በአርባምንጭ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች በተለያዩ መስኮች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መሰማራታቸው እንዳሚያስደስተው ገልፆ በክረምት ወራት ብቻ ሳይሆን ከዓመት ዓመት ባህል ሆኖ መቀጠል እንዳለበት አስረድቷል ። በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የህግ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት በረከት ማንዶሴ በበኩሉ እንዳለው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፉ ከአቻዎቹ የተለያዩ ልምዶች እንዲቀስም እድል ፈጥሮለታል ። ከዚህም ባለፈ ለሰዎች ጥሩ አመለካከት እንዲኖረኝና በማከናውናቸው ተግባራት የህሊና እርካታ እንዳገኝበት አድርጎኛል ብሏል ። በአርባ ምንጭ ከተማ የሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብርሃም እንዳሉት በ2011 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች በከተማዋ ተሰማርተዋል። በጎ ፈቃደኞቹ በጋሞ ብሄረሰብ ያለውን በጎ እሴት ተጠብቆ እንዲቆይና በመልካም ስነምግባር የታነጸ ትውልድ መፍጠር እንዲቻል ህብረተሰቡን በማስተማር ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው ። በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ በጽዳትና ውበት ጥበቃ ፣  በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት ፣ በትራፊክ ደህንነት ፣ በደም ልገሳ አገልግሎትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ባላቸው 16 የልማት መስኮች ተሰማርተው ህብረተሰባቸውን በማገልግል ላይ እንደሚገኙ ሃላፊው ተናግረዋል ። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተሳታፊዎች እያከናወኑ ያሉት ተግባር በገንዘብ ሲተመን ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው ተብሏል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም