በመቱ ከተማ በገበያ ዋጋ መናር መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለፁ

68
መቱ ሰኔ 6/2010 በመቱ ከተማ በግንባታ መሳሪያዎችና በምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመከሰቱ መቸገራቸውን  የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች  እንደገለጹት በከተማው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቆርቆሮ፣ ሚስማርና ቀለም   እንዲሁም በስንዴና ዱቄት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡ በከተማው 02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀማል ገምቴሳ እንዳሉት ከአንድ ወር በፊት በ40 ብር ሒሳብ ሲሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ሚስማር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ በ100 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የአንድ ቆርቆሮ ዋጋም ከወር በፊት ሲሸጥበት ከነበረው 150 ብር በአንድ ጊዜ ወደ  200 ብር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ “የዋጋ ጭማሪው ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ገዝቼ መጠቀም አልቻልኩም” ያሉት አቶ ጀማል ይህም በኑሮ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በከተማው 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ከግንባታ እቃዎች በተጨማሪ  የዳቦ ዱቄት፣ የፓስታና ማካሮኒ  ላይ በዚህ ሳምንት የዋጋ ጭማሪ ሲታይ በበርበሬና ነጭ ሽንኩርት ዋጋ ላይ ግን መጠነኛ ቅናሽ እንደታየ ተናግረዋል፡፡ 15 ብር ሲሸጥ የነበረው  አንድ ኪሎ የዳቦ ዱቄት በ19  ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በርበሬ ከ80 ብር ወደ 60 ብር ነጭ ሽንኩርት ደግሞ ከ40 ብር ወደ 25 ብር ዝቅ ብሎ እተሸጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የገበያ ዋጋ መናር በእለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረባቸው በመሆኑ መንግስት መፍትሄ እንዲፈልግለት ነዋሪዎቹ   ጠይቀዋል፡፡ በመቱ ከተማ በግንባታ መሳሪያዎች ንግድ የተሰማሩት አቶ ፉአድ ኢብራሂም  የግንባታ መሳሪያዎቹን ገዝተው ከሚያመጡበት ቦታ እስከ 50 ከመቶ ጭማሪ በመታየቱ ዋጋ ከፍ አድርገው ለመሸጥ እንደተገደዱ ይናገራሉ፡፡ በተለይ በቆርቆሮ፣ ሚስማርና ቀለም  ላይ ከፍተኛ ዋጋ በመጨመሩ  ነጋዴው ገዝቶ ለማቅረብ አቅም እንዳነሰውና ደንበኞችም ገዝተው ለመጠቀም እንዳልቻሉ ገልፀዋል። በስንዴና ዱቄት ማከፋፈል የተሰማሩት አቶ መኑ ብዛ  በገበያ ላይ ከስንዴ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የዳቦ ዱቄት  ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ በንግዱ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመቱ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢራቱ ሀብቴ  ስለሁኔታው ተጠይቀው በአንዳንድ የግንባታ እና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያቱን ለይቶ በማወቅ የክትትልና የቁጥጥር ስራ የሚያካሄድ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል ። በከተማው የሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡና ሽያጫቸውን በህጋዊ ደረሰኝ ብቻ መሆን እንደሚገባው ኃላፊው አሳስበዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም