አማራ እና በትግራይ አጎራባች አካባቢዎች በ93 ሚሊዮን ብር የልማት ስራ ይካሔዳል

55
ነሀሴ 8/2011 በአማራ እና በትግራይ አጎራባች አካባቢዎች ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ለማከናወን 93 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ገብረእግዚአብሄር ገብረዮሃንስ ለኢዜአ እንደገለፁት በጀቱ የተያዘው በሰቆጣ ቃል ኪዳን መሰረት በግብርናው ዘርፍ የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት ነው። በዚህም የመቀንጨር ችግር በሚስተዋልባቸው የአማራ እና የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚታየውን የስርኣተ ምግብና የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ተብሏል። በተመረጡ የሁለቱ ክልል አካባቢዎች ላይ በሚካሄደው ፕሮግራም በ93 ሚሊየን ብር በጀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዶሮና በፍየል እርባታ በመሳተፍ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ታቅዷል ። ለህብረተሰቡ የሚቀርቡት ዶሮዎችና ፍየሎች ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግም በባለሙያዎች የቅርብ ክትትል ይደረጋል ብለዋል ። በተያዘው በጀት 5 ሺህ 900 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አባወራዎችና እማወሯዎችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ደግሞ በሚኒቴሩ የእንስሳት ሃብት ዳይሬክቶሬት የወተት ሃብት ማደራጃና ማስፋፊያ ባለሙያ አቶ ዳባ ኦጀማ ናቸው፡፡ በተያዘው እቅድ መሰረትም መንግስት ከ 98 ሺህ በላይ የእርባታ ዶሮዎችና ከ12 ሺህ በላይ ፍየሎች ያከፋፍላል። በዚህም ህብረተሰቡ ከእንስሳት እርባታው የሚያገኘውን ወተትና እንቁላል ለምግብነት በማዋል የስርዓተ ምግብ ችግሮቻቸውን እንዲቀርፉ አስተዋፅኦ ከማበርከቱም ባለፈ የምግብ ዋስትና ችግራቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል ። የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደበበ አድማሱ እንዳሉት የስርዓተ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ የተቀናጀ የእንስሳት እርባታ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ፡፡ በግብርና ሚኒስቴር የታቀደውን የእንስሳት እርባታ ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ማስተባበሪያ የግብርና ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሙላት ተካ በበኩላቸው ስር የሰደደ የስርዓተ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ ሁሉን አቀፍ ቅንጅትና ርብርብ የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በአማራ እና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በ40 ወረዳዎች ስር የሰደደ የስርዓተ ምግብ እጥረት ወይም የመቀንጨር ችግር መኖሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም