ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚለውጥ የፈጠራ ውጤት ይፋ ተደረገ

112
አዳማ ኢዜአ/ ነሕሴ 08/2011 ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያና የእንስሳት መኖ ለመለወጥ የሚያስችል የፈጠራ ቴክኖሎጂ እውን ማድረጉን የአዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ገለጸ። የኮሌጁ ዲን አቶ ተሻለ ዱጉማ እንደገለጹት ቴክኖሎጂው በከተሞች የሚታየውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ችግር  ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነው ። ከፈጠራው ባለቤት ጋር በመሆን  እውን የተደረገው ቴክኖሎጂ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ለማስተላለፍ የዲዛይንና የማምረት አቅም ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል። ባለፈው የበጀት ዓመት ኮሌጁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን የሚረዱ 28 የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማውጣት ለጥቃቅንና አነስተኛ እንተርፕራይዞች ማስተላለፉን አመልክተዋል። በተያዘው አዲሱ የበጀት ዓመትም 30 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር ተለይተውና ፕሮጄክት ተቀርጾላቸው ተግባራዊ እንዲደረጉ ዝግጅት ተደርጓል ። የፈጠራው ባለቤት አቶ ዳምጠው ገመቹ በበኩላቸው ቴክኖሎጂውን ለመፍጠር ያነሳሳቸው በአዳማ ከተማ የሚታየውን  የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ በማሰብ ነው ብለዋል። በሙያቸው ጠበቃና የህግ ሰው የሆኑት አቶ ደምጠው ባላቸው ልዩ ተሰጥኦ ለአዳማ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የፕሮጄክቱን ዲዛይን በማቅረብ  እውን ማድረግ መቻላቸውን ተናግረዋል ። ቴክኖሎጂው በሰዓት እስከ ሶስት ኩንታል ደረቅ ቆሻሻ በመፍጨት ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያና የእንስሳት መኖ የመለወጥ አቅም ያለው መሆኑንም አመልክተዋል። የአትክልትና ፍራፍሬ ተረፈ ምርቶች፣ከቤት ውስጥ የሚወጣውን ደረቅ ቆሻሻ በቀላሉ ለማስውገድ፣ከተሞችን ፅዱ፣ውብና አሩንጓዴ ለማድረግ ጭምር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ከደረቅ ቆሻሻ ክምችት በሚወጣው ባክቴሪያና በካይ ጋዞች አካባቢያችን እየተበከለ ለጤና ችግር እየተዳረግን እንገኛለን ያሉት አቶ ዳምጠው ገመችስ ቴክኖሎጂውን ህብረተሰቡ ከ7 እስከ 10 ሺህ ብር አውጥቶ በመግዛት  በየቤቱ ሊጠቀምበት ይችላል ብለዋል። ሳይበሰብሱ ለረዥም ዓመታት የሚቀመጡ የውሃ መያዣ ፕላስቲክና ፌስታሎች ወደ ተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ምርቶች ለመለወጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመፍጠር የዲዘይን ሥራ እያጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም  ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አገልግሎት የሚውሉ ሌሎች አራት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር የፕሮፖዛል ጥናት እያጠናቀቁ መሆኑን አመልክተዋል። አዲሱን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ የፈጠራ ቴክኖሎጅ እውን ለማድረግ የአዳማ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ አርክቴክቸሮች ላደረጉላቸው ሙያዊ ድጋፍ አመስግነዋል። ለቴክኖሎጂው ፈጠራ ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የባለቤትነት መብትና የእውቅና ሰርትፍኬት አግኝተውበታል። ቴክኖሎጂው የሚፈጨውን ደረቅ ቆሻሻ ለማድረቅ ኖራ የሚጠቀም በመሆኑ የአርሶ አደሩ የእርሻ ማሳ ምርት እንዳይሰጥ እያደረገ ያለውን የአፈር አሲዳማነት ለመቀነስ የተፈጥሮ መዳበሪያው የላቀ ድርሻ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም