በሰሜን ሸዋ ዞን 30 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቶ እየተተከለ ነው

2897

ፍቼ ሰኔ 6/2010 በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ያገኘነውን   ውጤት ለማጠናከር  በተያዘው ክረምት የችግኝ ተከላ እያካሔዱ መሆናቸውን ገለፁ ።

የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት በበኩሉ 30 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላው ማቅረቡን አስታውቋል ።

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉ አርሶ አደሮቹ መካከል የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገመኔ ጫላ ”የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  ለግብርና ስራችን  ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ  በበጋና በክረምት ወራት በራሳችን ፍላጎትና ተነሳሽነት መስራታችን ተጠቃሚዎች አድርጎናል” ብለዋል ።

”በተለይ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ብለን የተከልነው ችግኝ የእርሻ መሬቱን ለምነት ከመጠበቅ ባሻገር ለእንሰሳት መኖ በበቂ ሁኔታ የምናገኝበት መልካም እድል እየፈጠረልን ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም  ተጠቃሚነታቸውን በበለጠ  ለማጎልበት በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር  ታዬ መኮንን በበኩላቸው  ባለፉት ዓመታት የተከሉትን የፍራፍሬ ችግኝ በመንከባከብ  የአፈር ለምነት ከመጠበቅ በተጨማሪ መጠነኛ ገቢ እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል ።

ይህንን  ስራ  ዘንድሮም አጠናክረው በመቀጠል  ችግኝ በብዛት ተክለው በእንክብካቤ ለማፅደቅ  እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል ።

ሌላው አስተያየት ሰጪ  አቶ ቶልቻ ዋቄ  እንዳሉት የችግኝ ተከላ ስራ  የአካባቢያቸውን ልምላሜ እንዲመለስ ያደረገ በመሆኑ ዘንድሮም በራስ ተነሳሽነት ጉድጓድ አዘጋጅተው  ችግኝ በመትከልና ነባሮችን  በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ባለፉት ዓመታት የተከሉት ችግኝ ፀድቆ አሁን ላይ ለንብ ማነብ አገልግሎት እየተጠቀሙበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  ሴት አርሶ አደር ቶለሺ   ለማ ናቸው ።

ይህንን ስራ በዘንድሮው ዓመት  አጠናክረው ለማከናወን  ከአካባቢያቸው ከሚገኝ ችግኝ ጣቢያ  ከ5 ሺህ  የሚበልጥ ችግኝ ተረክበው በማሳቸውና በአቅራቢያቸው በመትከል ላይ እንደሚገኙ  ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የእንሰትና ፍራፍሬ ችግኝ በጓሮአቸው በማልማታቸው ከቤት ውሰጥ የምግብና  የማገዶ ፈጆታ ባሻገር  ከ10 ሺህ ብር በላይ  ገቢ እንዳስገኘላቸው  ገልፀዋል ።

በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ ግርማ አሰፋ እንደገለፁት በ2ሺህ 500 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተዘጋጀ 30 ሚሊዮን ችግኝ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ ተከላ በመካሄድ ላይ ነው ።

በዞኑ13 ወረዳዎች በተራቆቱ 57 ሺህ 720 ሄክታር መሬት ላይ የሚተከለው ችግኝ አገር በቀል የዋንዛ ፣ የአበሻ ጥድ፣ የኮሶ፣ የወይራና የባህር ዘፍ ችግኝ በተጨማሪ ለከተማ ማስዋቢያ የሚውሉ የዛፍ አይነቶችን ያከተተ ነው፡፡

በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ከ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን  በላይ የፍራፍሬ ችግኝ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ባለፉት ሶስት ዓመታት በ28 ሺህ 683 ሄክታር መሬት ላይ የተከሉትን ችግኝ ከእንሰሳትና ከሰው ንክኪ በመጠበቅ በአሁኑ  ጊዜ ከ71 በመቶ በላይ መፅደቁን ተናግረዋል።