የትግራይና የአማራ አጎራባች ወረዳዎች የአሸንዳና ሻደይ በዓልን በጋራ ሊያከብሩ ነው

66
ነሀሴ 8/2011 የትግራይና የአማራ ክልል ዘጠኝ አጎራባች ወረዳዎች የአሸንዳ/ሻደይ በዓልን በጋራ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው። የበዓሉ ዋናው ባለቤት የሆኑት ልጃገረዶች፣የሚመለከታቸው አካላትና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት በዓሉን በጋራ ማክበራቸው በሁለቱም ክልል ሀዝቦች ለዘመናት የቆየውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ ነው። የትግራይ ማእከላዊ ዞን የቆላ ተምቤን ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሰ አብርሃ እንደገለፁት ከትግራይ ክልል ማእከላዊ ዞን አራት ወረዳዎችና ከአማራ ክልል ዋግኽምራ አምስት ወረዳዎች የተወጣጡ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች በጋራ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተዋል ። በተምቤን ዓብይዓዲ ከተማ በጋራ የሚከበረው የአሸንዳ/ሻደይ በዓል በሁለቱም ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ ህዝቦች የበዓሉን ቱሩፋቶች ተጠቅመው በመካከላቸው የቆየውን ግንኙነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ። በአማራ ክልል የዋግኸምራ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ አቶ ምስገናው መስፍን ለኢዜአ በስልክ በሰጡት አስተያየት የልጃገረዶች የነጻነት መገለጫ ተደርገው የሚታሰቡ የሻደይ/አሸንዳ በዓላት በጋራ ለማክበር መነሳሳት መፈጠሩ ተገቢነት አለው ብለዋል። የሁለቱን ክልል ህዝቦች የቆየ ፍቅርና አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑም የአጎራባች ወረዳዎች ነዋሪዎች በጋራ አብሮ የማክበር እሴቱን ለማጎልበት አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል። በዓሉን ለማየት ወደ አካባቢው የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችም የሃገራችንን ታሪክና ቅርስ እንዲያውቁ ለማድረግ መልካም አጋጣሚው እንደሚሆን ተናግረዋል። ከነሀሴ 15 ጀምሮ ለተከታተይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ላይ የሁለቱም ክልል ልጃገረዶች አቅምና ባህሉ በሚፈቅደው መሰረት ደምቀውና ተውበው ለዘመናት የቆየውን ግንኝነታቸው የሚያጠናክረበት መድረክ ነው ተብሏል ። በበዓሉ ላይ የሁለቱም ህዝቦች ባህልና ቋንቋ፤ታሪክና ማንነት የሚያንፀባርቅ ዘፈን ለማቅረብ መዘጋጀቱንም አስታውቋል። የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ህብረተሰቡ ዜጋ መልካም አስተሳሰብ የሚያሳይበትና በተግባር የሚያንፀባርቅበት እንዲሆንም አርቲስት መኳንት መልእክቱን አስተላልፏል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም