በሰሜን ወሎ ዞን 602 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰበሰበ

68
ወልዲያ ነሐሴ 8/ 2011  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሰሜን ወሎ ዞን ወጭን በራስ ለመሸፈን በተደረገ ጥረት 602 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ። በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ከ2010 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል። በመምሪያው የግብር ትምህርት ባለሙያ ወይዘሮ ኤልሳ ግርማይ እንደገለጹት በዞኑ የግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብር ለአገር እድገትና ልማትያለውን ፋይዳ እየተረዳ መጥቷል። በእዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ የገቢ አርዕስቶች ከ601 ነጠብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን በማሳያነት አቅርበዋል። የተሰበሰበው ገቢም ከዓመታዊ ዕቅዱ አንጻር ሲታይ 96 ነጥብ 6 በመቶ ለማሳካት እንደተቻለም ተናግረዋል። ባለሙያዋ እንዳሉት ግብሩ የተሰበሰበው 1 ሺህ 215 የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው 30 ሺህ 193 ከሚሆኑ ግብር ከፋይ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው። "በበጀት ዓመቱ ዞኑ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያወጣ ሲሆን ከ28 ነጥብ 2 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪ በተሰበሰበው ገቢ ለመሸፈን ተችሏል" ብለዋል። ከግብር ከፋዮች መካከል አቶ ደመቀ አሊጋዝ በሰጡት አስተያየት የመኝታ ክፍሎችን በማከራየት ከሚያገኙት ገቢ ከ39ሺህ ብር በላይ  ለመንግስት ግብር መክፈላቸውን ገልጸዋል። በከፈሉት ግብርም ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መካከል ምስጉን ግብር ከፋይ በሚል ሽልማት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። በዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ከፍተኛ የሒሳብ ባለሙያ አቶ ተስፋ መላኩ በበኩላቸው በግብር አስከፋዩና ግብር ከፋዩ መካከል በግብር ትመናና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚፈጠረውን ችግር ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየፈቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህም በዓመቱ ውጤታማ ገቢ በመሰብሰብ ዓመታዊ ወጭን ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ ማስቻሉን ነው የገለጹት።     ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም