የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ተቋማዊ የችግኝ እንክብካቤ ጥሪ አቀረበ

122
የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ሰራተኞች በክረምቱ የተከሏቸውን 6ሺ 100 ችግኞችን በየረር ደን መትከያ ጣቢያ ተገኝተው የእንክብካቤ ስራዎችን አከናውነዋል።
ተተክለው የመጽደቅ ዕድላቸው ዝቅተኛ የሆኑ ችግኞችን የመተካት፣ ሌሎችን የማረምና የመንከባከብ ተግባራት በሰራተኞቹ ተከናውኗል። ዛሬ በተከናወነው የመተካት፣ የማረምና የመኮትኮት ተግባር የመጽደቅ ዕድላቸው ዝቅተኛ በሆኑ 900 ችግኞች ፋንታ በአዲስ ችግኝ የመተካት ስራ ተሰርቷል። የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተቋማትና መላው ማህበረሰብ ተከታታይ ክትትልና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም በመላ አገሪቱ በተግባሩ ላይ ተሳታፊዎች የመንከባከቢያ ወቅት ከማለፉ በፊት ከወዲሁ መተካት ያለበትን ሁኔታ እንዲያረጋግጡ ኮሚሽነሩ አገራዊ ጥሪ አቅርበዋል። ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው ችግኝ ተተክሎ አፋጣኝ እንክብካቤ የሚደረግለት የተተከሉት ችግኞች መካከል የማይጸድቁ ካሉ ወቅቱ ሳያልፍ በፋንታቸው ለመተካት እንደሆነ ገልጸዋል። የእንክብካቤ ስራው ችግኙን ከሌሎች ጋር ተወዳድሮ ራሱን እንዲችልና ችግር የመቋቋም አቅም  እንደሚፈጥር ከወዲሁ ማረምና መኮትኮት ላይ መተኮር እንዳለበት አስገንዝበዋል። በቀጣይም ሁሉም በክረምት በየደረጃው የሚገኙ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ስራዎችን  መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ''በበጋም ውሃ  የማጠጣት ስራዎችን አካትተው እንደወቅቱ መንከባከብ አለባቸው'' ብለዋል። በእንክብካቤ ዘመቻው ላይ የተሳተፉ 100 የኮሚሽኑ ሰራተኞች በእንክብካቤ ወቅት ያልፀደቀ ችግኝ መኖሩን፤ እንደወይራ ያሉ የችግኝ ዝርያዎች በእንስሳት የመበላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ታዝበዋል። ሰራተኞችም ለችግኞች አለመጽደቅ ምክንያቱ በተከላ ወቅት ጉድጓዶቹ በአፈር ባለመሞላት ውሃ መያዛቸው ለችግሩን መንስኤ መሆኑን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም