ሚኒስቴሩ ለአገር ሰላምና ደህንነት ወጣቶች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበ

62
ነሐሴ 7/2011 በኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና አንድነትን በማስጠበቅ ለእድገትና በልፅግና በጋራ እንዲሰሩ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። የዓለም የወጣቶች ቀን በዓለም ለ20ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን የወጣቶች የንቅናቄ መድረክም ተካሂዷል። መድርኩ በአገሪቷ የሚወጡ ፖለሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና አሰራሮች ወጣቶችን ምን ያህል እየጠቀሙ ነው?፣ ምን ችግሮች አሉ የሚሉትና ሌሎች ጉዳዮች ተዳሰው መፍትሄ የሚፈልቅበትነው። የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የዓለም ጸጋይ እንደተናሩት፤ወጣቶች የአገርን ሠላምና አንድነት በማስጠበቅ እድገትና በልፅግና ለማምጣት መስራት አለባቸው። ወጣቶች በአገሪቷ የተፈጠሩ መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ለትውልድ የሚሸጋገር ሥራ በመስራት የዜግነት አሻራቸውን ማሳረፍ አለባቸው ብለዋል። ለአገሪቷ ገንቢ ሚና እንድኖራቸው በእውቀት፣ በክህሎትና ስነ ምግባር መታነፅ አለባቸው ያሉት ሚኒስትሯ ለዚህም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። ወጣቶች የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መንግስት የመደገፍን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ዋና ፀሀፊ ወጣት ኤርሚያስ ማቲዎስ እንደሚለው ኢትዮጵያ በጋራ መስራትና መደማመጥን የምትሻበት ወቅት ላይ ትገኛለች። በመሆኑም በመሳሪያ ሳይሆን በወረቀት፤ በግጭት ሳይሆን በንግግር ችግሮችን ለመፍታት ወጣቶች ዝግጁ መሆን አለባቸው ብሏል። በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ  የወጣቶች ሚኒስቴር ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ እንደሚናገሩት፤ ወጣቶችን በትምህርት መገንባትና በስነ ምግባር ማነፅ ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት። ወጣቶች አሉታዊ አስተሳሰቦችን በአወንታዊ በመቀየር አገርን የመገንባት ሚናቸውን በተግባር ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለባቸውም ነው ያሉት። በዕለቱ በአገሪቷ ወጣቶች ላይ የሚስትዋሉ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚያሳዩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የደም ልገሳና ኤግዚቪሽንም የመርሃ ግብሩ አካል ነበር። የዓለም የወጣቶች ቀን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት በመከበር ላይ ይገኛል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም