በአገራዊና በደቡብ ክልል ጸጥታና አደረጃጀት ጥናት ላይ የሚያተኩሩ መድረኮች ተጀመሩ

71
ሐዋሳ ነሐሴ 7 /2011  በአገራዊና በደቡብ ክልል ጸጥታና አደረጃጀት ጥናት ላይ የሚመክሩ የአመራሮች መድረኮች በሦስት ከተሞች እየተካሄዱ ነው። የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን)ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንዳስታወቀው መድረኮቹ በሐዋሳ፣ በአዳማና አዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ላይ ናቸው። የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገዛኽኝ ሜጎ በሐዋሳ እየተካሄደ ባለው መድረክ የደቡብ ክልል ማዕከል ተሿሚዎች እየተካፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአዳማ በተጀመረው መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። እንዲሁም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው መደረክ በፌዴራል ተቋማት የሚሰሩ አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል። ለአራት ቀናት በሚቆዩት መድረኮች በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው ለውጥና ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ አቅጣጫ ይቀመጥበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። በተጨማሪም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች መንስዔዎችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥም የቡድን ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመመለስ ድርጅቱ ባስጠናው ጥናት ላይ ውይይት እንደሚደረግ አቶ ገዛኽኝ አስታውቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም