በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ተግባር ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪን ማዳን እንደሚቻል ተገለፀ

64
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 በመዲናዋ በሚደረጉ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በዚህ ክረምት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወጪን ማዳን እንደሚቻል ተገለጸ። 16ኛውን የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቅድመ ዝግጅትን በማስመልከት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዋናነትም ደም በመለገስ፣ የተለያዩ የትራፊክ አገልግሎቶችን በመስጠት፣ ችግኞችን በመትከልና የክረምት ትምህርት በማስተማር በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ለማዳን እንደሚሰራም ነው የተገለጸው። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት አባይነህ አስማረ በዚሁ ወቅት እንደተናገረው፤ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እርዳታና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍል ለይተው በማገዝ የተለመደውን የመልካምነት ተግባር ማስቀጠል ይገባቸዋል። በተለይ የትራፊክ አደጋን ተከትሎ የደም እጥረት ስለሚፈጠር ይህን ችግር  በዘላቂነት ለመፍታት በዘንድሮው የበጎ ፍቃድ ተግባር ውስጥ ደም የማሰባሰብ ስራ በሰፊው ሊሰራበት እንደታሰበም አክሎ ገልጿል። የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወጣት አለምፀሀይ መንግስቴ በበኩሏ፤ የበጎ ፍቃድ ተግባር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተሳታፊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ በማለቱ ባለፈው  ዓመት ከ 820 ሺህ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጻለች። ይህም ቁጥር የሚያመላክተው የበጎ ፍቃድ ስራ በሌሎች የህብረተሰብ ክፍል ውስጥም ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም በመንግስትና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊወጣ የነበረ 50 ሚሊዮን ብር ሀብት ማትረፍ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡ በዘንድሮ ዓመት ሰፊ የወጣቶች  ቁጥር ያቀፈ የክረምት የበጎ ፍቃድ ተግባር ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ እንደሚከናወን ይጠበቃል። የህብረተሰቡ ችግር የኔ ችግር ነው፤ ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም ሰው በተለይ ወጣቱ 'ሰውን ለመርዳት ሰው ብቻ ሆኖ መገኘት በቂ በመሆኑ' በዚህ የበጎ ፍቃድ ስራ ላይ መሳተፍ እንደሚገባም ተጠቁሟል። በመዲናዋ 12  ዓይነት የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ለማከናወን የታሰበ ሲሆን፤ ወጣቶቹ በአደረጃጀቶች ተከፋፍለው እንደሚሰሩም ተገልጿል። ዘንድሮ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችንና በጎ ፈቃደኛ የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፉበት ሲሆን፤ የቁጥሩ መጨመር አገልግሎቱ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተሻለ መልኩ ለመደገፍ እንደሚረዳም ነው የተገለጸው። በተጨማሪም የተመረጡ የከተማዋን ቦታዎች  የማስዋብ ስራ ከታቀዱት ተግባራት አንዱ ነው ተብሏል። የበጎ ፍቃድ ተግባር በተለይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እየተለመደ እንደመጣ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያም ይህን ተሞክሮ ከሌሎች አገራት በመውሰድ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት አገልግሎቱን በማስተዋወቅ በአሁኑ ሰዓትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የበጎ አድራጊዎችን በማፍራትና መልካም ተግባሮችን በመፈጸም ተግባሩን ማስቀጠል ችላለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም