የኤሌክትሪክ ኃይል ከአንድ ወር በላይ በመቋረጡ በሥራቸው ላይ ጫና ፈጥሯል....የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች

52
ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ነሀሴ 7 ቀን 2011 የኤሌክትሪክ ኃይል ከአንድ ወር በላይ በመቋረጡ በእለት ተዕለት ሥራቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። በከተማው የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ አንዷለም ተመስገን ለኢዜአ እንዳሉት በቀበሌው የሚገኘው ትራንስፎርመር ከሰኔ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመቃጠሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል። ይህም የዕለት ተዕለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢያቸው ጨለማን ተገን በማድረግ የዝርፊያ ወንጀል እየተባባሰ እንዲመጣ ማድረጉን አመልክተዋል። በቀበሌያቸው ከ700 በላይ አባውራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አለመሆናቸውን ገልጸው “እስከ ዞን አስተዳደር ድረስ ሄደን ችግሩን ብናሳውቅም መፍትሔ ማግኘት አልቻልንም” ብለዋል። የቀበሌ 01 ነዋሪ ወጣት ዮናስ ጌትነት በበኩሉ ከመንግስት ብድር በመውሰድ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ በቢሮ እቃዎች ማምረት ሥራ ቢሰማራም በኢሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ለኪሳራ መዳረጉን ነው የገለጸው። “በእዚህም በሳምንት መጣል ያለብኝን የአንድ ሺህ ብር እቁብ መክፈል ባለመቻሌ ለማቋረጥ ተገድጂያለሁ” ብሏል ችግሩን በተደጋጋሚ ለመብራት ኃይል በማሳወቅ በተቃጠለው ምትክ ትራንስፎርመር ቢተካም ኃይል የሚያገኙት በፈረቃ መሆኑንና ይህም በየደቂቃው ስለሚቋረጥ ስራውን መስራት እንዳልቻለ ተናግሯል። የቀበሌ 03 ነዋሪ ወይዘሮ አባይ ጫላ በበኩላቸው በመብራት መጥፋት ምክንያት እንጀራና ዳቦ ጋግረው ይተዳደሩበት የነበረውን ሥራ ማቋረጣቸውን ተናግረዋል። በሰፈራቸው የነበረው ትራንስፎርመር በተደጋጋሚ መጥፋት የጀመረው ከሦስት ዓመት በፊት ስለነበር እንዲቀየር በአካባቢው ላለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በየጊዜው ሲያመለክቱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። ካለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ አንስቶ ትራንስፎርመሩ ሙሉ በሙሉ ስራ በማቆሙ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡንና መቸገራቸውን ገልፀዋል። የማገዶ ወጭ ከፍተኛ በመሆኑም ስራውን በማቆም ችግር ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመዋል። የኤትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደብረ ማርቆስ ዲስትሪክት ተወካይ ኃላፊ አቶ መላኩ ዳኛቸው በበኩላቸው በአካባቢው በፊት የነበረው ትራንስፎርመር ከተጠቃሚው ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በተፈጠረበት ጫና መሸከም ባለመቻሉ መቃጠሉን ገልፀዋል። ከተቃጠለው ትራንስፎርመር የተሻለ አቅም ያለውና ከፍ ያለ ኃይል መስጠት የሚችል ትራንስፎርመር ለመተካት በሀገር አቀፍ ደረጃ እጥረት በመኖሩ የህብረተሰቡን ጥያቄ ፈጥኖ ለመፍታት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። የተቃጠሉ ትራንስፎርመሮች ተጠግነው በፍጥነት አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን አመልክተዋል። በጊዜያዊነት በፈረቃ መጠቀም የሚያስችላቸውን ባለ100 ኪሎ ዋት ትራንስፎርመር በመተካት ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቀሰዋል። የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው በቂ ኃይል ሊሸከሙ የሚችሉ ትራንስፎርመሮች እጥረት ችግሩ እንዲከሰት ማድረጉን ገልጸዋል። ችግሩ በደብረ መናርቆስ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም እንደሚስተዋል ጠቅሰው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም