የማህበር ገንዘብ ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

65
ሀረር ሰኔ 6/2010 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሚደጋ ቶላ ወረዳ ከ130ሺ ብር በላይ የማህበር ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ ሶስት ተከሳሾች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ  የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይዎች ዲቪዠን ሃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፉ ዛሬ ለኢዜአ እንደለጹት በሚደጋ ቶላ ወረዳ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ ፣የሒሳብ ሰራተኛና ገንዘብ ያዥ ላይ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው የሕዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋላቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ነው። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ የነበረው አደሜ ሼህ ኡመር፣ የሒሳብ ሰራተኛው በድሩ ያሲን መሐመድና ገንዘብ ያዡ  አቶ አልይ አሜ በከር ከየካቲት 15 ቀን 2008 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ከተበዳሪ አርሶ አደሮች ከተመለሰ አንድ ሚሊዮን 400ሺ 48 ብር ውስጥ 139ሺ 300 ብር ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ገልፀዋል። አርሶ አደሮች ባደረባቸው ጥርጣሬ እንዲጣራ ለወረዳው ባመለከቱት መሠረት ወረዳው ጉዳዩን ለኦሮሚያ ክልል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የምስራቅ ቅርንጫፍ አቃቢ ህግ ያስተላልፋል። በጥቆማው መሰረትም የምርመራ መዝገቡን የማየት ስልጣን ላለው ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተላልፎ ተከሳሾቹ ወንጀል መፈጸማቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ ተከሳሾቹ ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ያለአግባብ ጥቅም ለማግኘት ሆን ብለው ድርጊቱን መፈጸማቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል። ፍርድ ቤቱም ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ የነበረው አደሜ ሼህ ኡመር በአምስት ዓመት እስራትና 3ሺህ ብር፤ 2ኛ ተከሳሽ በድሩ ያሲን መሐመድ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራትና 2ሺ ብር ቅጣት እንደተወሰነባቸው ተናግረዋል፡፡ ሶስተኛው ተከሳሽ  አልይ አሜ በከር ደግሞ በሶስት ዓመት እስራትና ሶስት  ሺህ ብር እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ኮማንደር ስዩም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም