ስምምነቱ ጥቅማችንን የሚጎዳ ነው ሲሉ የአዲ ፀፀር ነዋሪዎች ተቃውማቸውን ገለጹ

87
ሽሬ እንዳስላሴ ሰኔ 6/2010 የአልጀርሱ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመቀበል የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ያስተላለፈው ውሳኔ "ለዘመናት የኖርንበት መሬት ለኤርትራ አሳልፈን በመስጠት ጥቅማችንን የሚጎዳ በመሆኑ እንቃወማዋለን" ሲሉ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የአዲ ፀፀር ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ። ነዋሪዎቹ  ትናንት ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተወካዮቻቸው በኩል  እንዳሉት ስምምነቱ መሬታቸውን ለኤርትራ ተላልፎ የሚሰጥ ነው፡፡ የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት የነዋሪዎች ተወካይ አቶ ገብረፃዲቅ ገብረማርያም ባደረጉት ንግግር" እድሜ ልኬን በዚሁ በአዲ ፀፀር የገጠር ቀበሌ ኖሬያለሁ፤አንድም ቀን ይህ መሬት የኤርትራ ነው ተብሎ አይታወቅም " ብለዋል፡፡ አሁን ለኤርትራ ይሰጣል መባሉ ነዋሪዎችን እንዳስቆጣ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ተወካይ ወይዘሮ ትእበ ተሰፋ ማርያም በበኩላቸው "ኢህአዴግ  ለዘመናት የኖርንበት መሬት ለኤርትራ አሳልፎ ይሰጣል የሚል እምነት ባይኖረኝም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ግን ከነዋሪው ጋር መመካከር አለበት" ብለዋል። የአልጀርሱ ስምምነት ዘላቂ ጥቅማቸውን እንደሚጎዳ በመግለጽ እንደሚቃወመው የተናገረው ደግሞ የሰልፉ ተሳታፊ  ወጣት ጎይቶኦም ግድይ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ የቀበሌው ነዋሪዎች ተሳታፈ በሆኑበት  ሰላማዊ ሰልፍ  ተቋውሟቸውን መፈክሮችን በማሰማት ጭምር ገልጸዋል። የባድመ ከተማ ነዋሪዎች በተመሳሳይ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ቀደም ሲል ተዘግቧል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም