በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 35 ሺህ 555 ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን እየተሰራ ነው

1490

ደብረ ብርሃን ሰኔ 6/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት 35 ሺህ 555 ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን የሚያስችል ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የጥምር ደን እርሻ ባለሙያ አቶ ኤፍሬም እሸቴ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ 945 ተፋሰሶች የሚገኘውን ይህንኑ መሬት በደን ለመሸፈን 350 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል፡፡

ከተዘጋጀው ችግኝ ውስጥ 75 ሚሊዮኑ ለእንስሳት መኖ የሚውል ሲሆን ቀሪው  የጽድ፣ ወይራ፣ ነጭና ቀይ ባህርዛፍ፣ ዋንዛ ግራቪሊያ፣ ግራርና ሌሎች የደን ዝርያዎች ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም ለችግኝ ተከላ የሚሆን ጉድጓድ ቁፋሮ በአርሶ አደሮች በመካሄድ ላይ ሲሆን እስካሁን 623 ሺህ 400 ጉድጓድ ተቆፍሯል፡፡

የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

በተያዘው ክረምት የሚተከለው ችግኝ  የዞኑን የደን ሽፋን አሁን ካለበት 15 ነጥብ 2 ከመቶ ወደ 16 ነጥብ 2 ከመቶ ለማድረስ እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከለው 212 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 191 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኝ መጽደቁን ጨምረው ገልፀዋል፡፡