በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጎሮ ሙጢ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

65
ሀረር ሰኔ 6/2010 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጎሮ ሙጢ ወረዳ ትላንት ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በአደጋው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በስምንት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዢን ኃላፊ  ኮማንደር ስዩም ደገፋ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ከጎሮ ሙጢ ከተማ ወደ ጨለንቆ ከተማ ከእቃ ላይ  ሰዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር  ኮድ 3 – 2003 አይሱዙ  የጭነት መኪና በወረዳው ጨፌ አነኒ ቀበሌ ሲደርስ  መንገዱን ስቶ በመገልበጡ ነው፡፡ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በጨለንቆና ድሬዳዋ ድልጮራ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቷል፡፡ ከፍተኛ ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም መንስዔ የሆነውን  ህዝብን በጭነት መኪና የማጓጓዝ ስራን ለመቅረፍ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ  የተለያዩ ተግባራትን ቢያከናውንም ህብረተሰቡ ግን ከእንቅስቃሴው ሊታቀብ እንዳልቻለ ገልጸዋል። በቀጣይም ህብረተሰቡ ለህዝብ ባልተፈቀደ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ ትራሰንፖርት መጠቀም አደጋው የከፋ መሆኑን አውቆ ጥንቃቄ ማድረግ  እንዳለበት ተናግረዋል። በምስራቅ ሐረርጌ  ዞን በአንድ ወራት ውስጥ በደረሱ ሶስት የትራፊክ አደጋዎች የ18 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ22 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን  ኮማንደር ስዩም አክለው ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም