የድሬዳዋን የአንድነት መገለጫ እሴቶች ለመመለስ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

97
ድሬደዋ  ነሐሴ 5/2011 የድሬዳዋን የፍቅር ፣የሰላምና የአንድነት መገለጫ እሴቶች ለመመለስ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡ “አንድ ዕድል ለሰላም”  በሚል መሪ ሃሳብ የዛፍ ጥላ ሥር  የእርቅ ሰላም ውይይት  በድሬደዋ ተካሄዷል። በውይይቱ ተሳተፉት ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት ድሬዳዋ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖርባት የፍቅር አርአያ ናት፡፡ ይህ ለሀገር አርአያ የሆነውን ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለመሸርሸር የሚደረገው ጥረት ቦታ እንደሌለው  ገልጸዋል፡፡ የድሬዳዋ  አርአያዊ አንድነትን ለመጠበቅና በትውልድ ውስጥ የትላንቱን ታላቅ የህብረት ስብዕና ለመመለስ ሁሉም  ኃላፊነቱን እንዲወጣ አመልክተዋል፡፡ በተለይ ትናንት በዛፍ ጥላ ሥር የተጀመረውን የውይይት ባህላዊ እሴት በማጎልበት የድሬዳዋን የፍቅር  መገለጫ እሴቶች ለመመለስ የተዋቀረው የአባቶች የሰላም ኮሜቴ ወሳኝ መሆኑን  ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት እንደ የክቡር ዶክተር አሊ  መሐመድ ቢራ እና እንደ የክቡር ዶክተር አሊ ሸቦ ኮሚቴውን በማገዝ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሀገሪቱ የሰላም አያያዝ በአስተማማኝ መንገድ እንዲጠበቅና እሷም ሆነች  ሌሎቹ ወገኖቿ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የዛፍ ጥላ ሥር  ውይይት  እንዲካሄድ ሃሳብ ባቀረበችው መሰረት መጀመሩን  የተነገረችው እንደአውሮፓ አቆጣጠር  የ2019 የአልም የማህበረሰብ አገልግሎት ሚስዝ ወርልድ አሻናፊና የድሬዳዋዋ ተወላጅ ፈቲሃ መሐመድ ናት፡፡ የድሬዳዋን  ፍቅርና አንድነት ለመመለስ የተጀመረው ውይይት  በቀጣይ  በሌሎችም ለሀገሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግ ገልጻለች፡፡ በዛፍ ጥላ ሥር በተካሄደው   ውይይት  የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው “ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና ፍቅር ለመጠበቅ ባህላዊ የሽምግልና እሴቶችን በሥራ ላይ ማዋል ይገባል “ብለዋል፡፡ የሀገሪቱ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ውስጥ ለሀገርና ለአለም የሚተርፍ ባህላዊ የሽምግልና እሴቶች እንዳሉ ተናግረው  እነዚህን  ተግባራዊ ማድረግ  ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ለነዚህ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ትኩረት ተደርጎ  የሀገሪቱ ሰላምና የህዝቦችን አንድነት አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ “በተለይ እነዚህን እሴቶች ለወጣቱ  በማውረስ የሀገሪቱን ሰላም እና ዕድገት የሚጠብቅ የሰከነ ትውልድ መፍጠር ላይ መረባረብ ይገባል”ብለዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፈው የክቡር ዶክተር  አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራ  ሁሉንም አቃፊና ደጋፊ የነበረው  የድሬዳዋን አንድነት ፣ ሰላምና መተባበር እሴቶች ወደ ነበረበት ለመመለስ ከሌሎች ጋር በመሆን እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ “ሃሳቡን ያመጣችውን ፈቲሃ መሐመድን አደንቃለሁ፤ እኛም በምንጓዝበት ቦታ ሁሉ ይህን የድሬዳዋን ህብረት ለመመለስ ኃላፊነታችንን እንወጣለን “ብሏል፡፡ በዛፍ ጥላ ስር ውይይት የተሳተፉት የእርቀ ሰላም  ኮሚሽን  ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ድሬዳዋ የፍቅር አርማና የአንድነት መገለጫ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ “ሁለቱም ኃይማኖቶች በተመሣሣይና በእኩል መንገድ የሚስተናገዱበት ከተማ መሆን አለበት”  ያሉት ወይዘሮ የትነበርሽ ድሬ ግቡ እንጂ ውጡ የሌለባት ከተማ በመሆን አርአያነቷን ማሳየት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡በውይይቱ  የተሳተፉ ምሁራንና  የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የድሬዳዋን ብሎም የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት በአስተማማኝ መንገድ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም የዛፍ ጥላ ሥር ውይይት የሚያስቀጥሉ፣ ለሚፈጠሩና ለተፈጠሩ ግጭቶች በባህላዊ መንገድ ዕርቅ መፍጠር የሚችሉ ከሁሉም መስክ የተውጣጡ አባላት ያሉበት የአባቶች የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የኮሚቴው አባላት  የድሬዳዋ የፍቅርና አንድነት ወደነበረበት ለመመለስና የሀገሪን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል፡፡ ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማት ተበርክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም