“የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ እንቅስቃሴ የህዝቦችን አገራዊ ስሜት የሚያነቃቃና አንድነትን የሚያጠናክር ነው”- አባት አርበኞች

83
አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/ 2010 "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ብሄራዊ መግባባትን በማጠናከር የተሻለ ሁለንተናዊ አንድነትን ለመፍጠር በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አቅጣጫዎች የጀመሩት ጥረት የዜጎችን አገራዊ ስሜት የሚያነቃቃ በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባው ነው" ሲሉ አባት አርበኞች ተናገሩ። በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመት የቆየው የጣሊያን ወረራ በጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች ትግል አገሪቱን ለቆ የወጣበት የጀግኖች አርበኞች መታሰቢያ  77ኛ ዓመት ነገ በመላው ኢትዮጵያ ይከበራል።  ቀኑን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው አባት አርበኞች እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ከተረከቡበት ማግስት ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ  ክፍሎች እያካሄዱ ያለው ጉብኝትና ህዝባዊ ውይይት በአገሪቱ ህዝቦች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረውን ያለመረጋጋት ስጋት በእጅጉ የቀነሰ፤ እየተፈጠረ የመጣውን ቅራኔ ያረገበ ነው። ዶክተር አብይ በአሁኑ ወቅት በትኩረት የሚያከናውኑት ተግባር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ  እንድትመጣ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይስተዋሉ የነበሩት መከፋፈልና ግጭቶች የአገሪቷን አንድነትና ህልውና አደጋ ውስጥ ከተው እንደነበር ነው አባት አርበኞቹ የሚናገሩት። የተጀመረውን መልካም  ጉዞ ከግብ ለማድረስ   የወጣቶች፣ የወላጆችና የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነትም ጉልህ መሆን አለበት ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የአውሮፓ ቀኝ ገዢ ኃይሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮችን በኃይል ሲቆጣጠሩ እምቢተኝነቷን በማሳየት በአባት አርበኞች የህይወት መስዋዕትነት ነጻነቷን ያስጠበቀች አገር መሆኗ ዓለም የሚያወሳው ታሪክ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም