የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል- የእስልምና እምነት ተከታዮች

69
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች ተናገሩ። ባለፈው ግንቦት 9 ቀን 2010 የጀመረው 1439ኛው ዓመት የረመዳን ፆም የፊታችን ዓርብ ወይም ቅዳሜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። የረመዳን ወር ምእመናን ጥልቅ  መንፈሳዊነት የሚያንፀባርቁበት፣ ራሳቸውን ለፈጣሪ የበለጠ የሚያስገዙበት፣  ከመቼውም ጊዜ የላቀ ደግነትና ቸርነት የሚያሳዩበት ቅዱስ ወር እንደሆነ የእምነቱ ሊቃውንት ይገልፃሉ። የእምነቱ ተከታዮች በሰጡት አስተያየት፤ በየዓመቱ በጉጉት በሚጠበቀው በዚህ የረመዳን ወር በኢስላማዊ አስተምህሮት መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ለሁሉም የሰው ፍጡር እዝነትን በመቸር ጭምር እያከናወኑ ነው። መስጂዶች በተለየ መንገድ በምእመናን በተጨናነቁበት በዚህ ወር የእምነቱ አባቶች ስለሰላም፣ አብሮ መኖርና መቻቻል ከመስበክም በላይ  ጸሎት አድርገዋል። የዘንደሮው የረመዳን ፆም በሰላምና እየተጠናቀቀ መሆኑን የሚገልፁት አስተያየት ሰጪዎቹ ፍፃሜውን ተከተሎ የሚመጣውን የኢድ-አልፈጥር በዓልንም በመረዳዳትና በመተዛዘን መንፈስ እንደሚያከብሩት ተናግረዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ መህዲ ሁሴን፤ እንዳሉት፤ መላው ሙስሊም በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ፣ ህሙማንን በመጠየቅ፣  ስለአብሮ መኖርና መቻቻል በመስበክ ሊሆን ይገባል። ''ሰደቃ በማብዛት ሁሉም በመተዛዘን በመተባበር ያለውን በመስጠት የታረዘውን በማልበስ ያለውን በማካፈል በሰላም የተጀመረው የረመዳን ወር  ኢዱንም በጥሩ ሁኔታ በመተባበር፤  በመተዛዘን ፤ በዚህ አይነት ሁኔታ ነው ማለፍ ያለበት  ˝ ያሉት አቶ በሽር ሊቨን ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም