በአፋር ክልል ተከስተው የነበሩ የኩፍኝና የኮሌራ በሽታዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

65
ሰመራ (ኢዜአ) ነሀሴ 4 / 2011 በአፋር ክልል ተከስተው የነበሩት የኩፍኝና የኮሌራ በሽታዎች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለፀ ። በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አብዱ አሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በክልሉ በአውሲ-ረሱ ዞን በሚገኙ 3 ወረዳዎች 16 ቀበሌዎች ላይ ተከስቶ የነበረው የኩፍኝ በሽታ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏል ። በሽታው ተከስቶባቸው የነበሩት የአይሳኢታ፣ ዱብቲና አፋምቦ ወረዳዎች ሲሆኑ 548 ሰዎች በበሽታው ተይዘው 5 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን አስታውሰዋል ። በሰኔ ወር መጨረሻ በገቢ-ረሱ ዞን አሚበራ ወረዳ ተከስቶ በነበረውም የኮሌራ በሽታም 157 ሰዎች ተይዘው በህክምና ሲድኑ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ገልፀዋል ። ክልሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ክትባት በመስጠት፣ የአካባቢ ጽዳት በመጠበቅና በጥንቃቄ ዙሪያ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ትምህርት ተደራሽ በማድረግ በሽታዎቹን በቁጥጥር ስራ ማዋል እንደተቻለ አስረድተዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኩፍኝ በሽታ ተከስቶ በነበረባቸው ሦስቱ ወረዳዎች አንድም በሽተኛ አለመመዝገቡንና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሳይስፋፋ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስተባባሪው ተናግረዋል ። "በኮሌራ በሽታም በዚህ ሳምንት ውስጥ ምንም አይነት በሽተኛ አልተመዘገበም" ብለዋል ። የኬሌራ በሽታን ሰርጭቱን ለመከላከል በወረዳው ለሚገኙ 50 ሺህ 190 ሰዎች ክትባት ተሰጥቷል። ሁለቱንም በሽታዎች ተመልሰው እንዳያገረሹ በሁሉም ወረዳዎች የቅድመ ክትትልና የቅኝት ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ከአስተባባሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም