ለመረጃ ተደራሽነት የተለየ አጽንኦት ሰጥቶ መስራት ይገባል-የመንግስት ኮሙኒዩኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት

61
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 የፌዴራል ህዝብ ግንኙነት ተቋማት ለመረጃ ተደራሽነት የተለየ አጽንኦት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ። ጽህፈት ቤቱ መረጃን ተደራሽ ከማደረግ አንፃር በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገምና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት  እንደገለጹት "የፌዴራል ህዝብ ግንኙነት ተቋማት ለህብረተሰቡ የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በአጽንኦት መስራት ይኖርባቸዋል"። የመረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ህብረተሰቡ በአገሩ ጉዳይ ላይ ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆንና በአገር ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ከማስቻሉም በላይ፤ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ያደርጋል ብለዋል። በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሚዲያዎች ተከታታይ መረጃ መስጠትና "የመንግስትን አቋም የሚተነትኑ መግለጫዎችን ተደራሽ ማድረግ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ነበሩ" ብለዋል። ህብረተሰቡ በሰላም ግንባታ ሂደት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ መልዕክት ቀርጾ ማስተላለፍ፣ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ሁነቶችን በማስተባበር ለጋራ መግባባትና ገጽታ ግንባታ ማዋል፣ የህዝብ አስተያየት ዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ጥቅም ላይ ማዋልና የዘርፉን አመራርና ባለሙያ አቅም መገንባት ሌላው በትኩረት የተሰሩ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል። በአገሪቷ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለመረጋጋትና የጸጥታ ችግሮች ተከስቶ በነበረበት ወቅት ግን በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት መዋቅሮች በተደራጀና ግንባር ቀደም በመሆን ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ፈጣን መረጃ ከመስጠት አንፃር ሰፊ ውስንነቶች ነበሩባቸው ብለዋል ሚኒስትሩ። አሁን የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ዘላቂነት እንዲኖረውና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና የህግ የበላይነት የሰፈነባት አገር ለመገንባት በመረጃ የበለጸገና በሁሉም መስኮች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የሚችል፤ ምክንያታዊ አስተሳሰቡ የጎለበተ ህብረተሰብ መፍጠር ይጠይቃልም ነው ያሉት። የህዝብ ግንኙነት ተቋማት በመረጃ የበለጸገ ህብረተሰብ መፍጠር ዋና ተግበራቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም