የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

84
ነሃሴ 3/2011 ለውጡ ህዝቡ በሚፈልገው ደረጃ እንዲሄድ ማድረግ ላይ  የአመራሩ  ቁመና ያለበትን ደረጃ  በዝርዝር መገምገሙን  የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ  ገለጹ፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላለፉት ሁለት ቀናት ያካሄደውን ግምገማ አጠናቋል፡፡ በአመራር ደረጃ የተያዘውን ለውጥ በማስቀጠል ሀገሪቱን ወደፊት ለማስኬድ የሚሰሩ  እንዳሉ ሁሉ  በተቸካይነት፣ በዘገምተኝነትና የቀድሞውን ይዞ የመቆዘም የመሳሰሉ ድክመቶች እንደነበሩ  የስራ አስፈጻሚው መገምገሙን አቶ ፍቃዱ ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም  ለውጡን  የሚመራው አመራር በተሻለ መደማመጥና ሃላፊነት መስራት እንደሚገባው  አቅጣጫ  መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ የስራ አስፈጻሚው  በድርጅቶች  መካከል አንድነትን የሚጎዱ አካሄዶች እንዲታረሙ  በግልጽ በመገምግም የማስተካከያ  አቅጣጫ ማስቀመጡንም አስረድተዋል፡፡ ለህዝብ ተጠቃሚነት ፣ለሰላም ፣ለህግ የበላይነትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተሰሩ ተግባራትን እያንዳንዱ ድርጅት ማየት እንዳለበትም ከድምዳሜ ላይ መደረሱን አቶ ፍቃዱ አንስተዋል፡፡ የህግ የበላይነት ማስከበርና የለውጡን ሪፎርሞች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው መስራት እንደሚያስፈልግ  አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡ በ2012 የሚካሄደው የሀገር አቀፍ ምርጫ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲካሄድ  እንደ ድርጅትም ሆነ እንደ መንግስት ዝግጅት እንዲደረግ ውሳኔ ላይ መደረሱን  አቶ ፍቃዱ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም