የዛፍ ጥላ ሥር ውይይት ነገ ድሬዳዋ ይካሄዳል

447

ድሬዳዋ ኢዜአ ነሐሴ 3/2011  “ አንድ ዕድል ለሰላም “ በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የዛፍ ጥላ ሥር ውይይት ነገ በድሬዳዋ አስተዳደር እንደሚካሄድ የአስተዳደሩ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

በውይይቱ የሚስዝ ወርልድ 2019 አሸናፊ ፣የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊቢራና ሌሎችም ተዋቂ ሰዎች እንደሚሳተፉም ተመልክቷል።

ፕሮግራሙን አስመልክተው የድሬዳዋ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ዛሬ እንደተገለጹት ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ባህሎችን በመጠቀም ሽምግልና በአካባቢና በሀገር ሰላም ዘላቂነትን ላይ ያለውን ሚና በትውልድ ውስጥ ማስረጽ ነው፡፡

የዛፍ ጥላ ስር ውይይትን በመጀመርና ተቋማዊ አደረጃጀትን በማኖር  ከባቢያዊ ግጭቶች በመከላከል ሀገር አቀፍ ሰላም እንዲረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

“ነገ በአርአያነት በሚጀመረው ውይይት ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ታዋቂ አርቲስቶች፣ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞችና አባገዳዎች፣ የፌደራልና የክልል አመራሮች ይሳተፋሉ “ብለዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ከውይይቱ በኋላ ገለልተኛ የድሬዳዋ የሰላም አባቶች አደረጃጀት ይፈጥራል፡፡

የድሬዳዋ ተወላጇ የውይይቱ መነሻ ሃሳብ ባለቤትና በላስቬጋስ አሜሪካ በተካሄደው የሚስዝ ወርልድ 2019 አሸናፊ የሆነችው ሞዴሊስትና የፋሽን ባለሙያ ፈቲሃ መሐመድ በበኩሏ በልዩነት ውስጥ የተገነባውን የማይበጠስ አንድነት ወደነበረበት ለመመለስ በማሰብ ሃሳቡ ወደተግባር እንዲለወጥ መነሳቷን ተናግራለች፡፡

“እየላላ ያለውን ይህን ህብረት ወደ ቦታ ለመመለስና የራሳችን ችግር በራሳችን በመፍታት ሰላማችን በዘላቂነት ለመጠበቅ የዛፍ ጥላ ውይይት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው “ብላለች፡፡

ድሬዳዋ በፍቅርና በአንድነት የተገነባው ስብዕና ለመላው ሀገሪቱ በምሳሌነት እንዲያገለግል  ወደ ቀድሞ መገለጫዋ ለመመለስ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ሚስዝ ውርልድ ፈቲሃ አመልክታለች፡፡

በውይይቱ እንደ የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊቢራ የመሳሰሉ ታዋቂ ሰዎች፣ከባህልና ቱሪዝም እና ከሰላም ሚኒስቴሮች የሚመጡ እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል።