በቤንች ሸኮ ዞን ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር የተሳተፉ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እየሆኑ ነው

65
ሚዛን (ኢዜአ) ነሀሴ 3 ቀን 2011  በቤንቺ ሸኮ ዞን ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር በመሳተፍ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑ ተገለፀ ። ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ በቤንች ሸኮ ዞን ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር በመሳተፍ  በሰው ግድያ፣ የአካል ጉዳት  በማድረስ፣ ንብረት በማውደምና ዘረፋ በመፈጸም ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እየተደረጉ ነው ። የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥና የኮማንድ ፖስት አባል ዋና ኢንስፔክተር ምናሉ ታደሰ እንደገለፁት ከ100 በላይ ተጠርጣሪዎች  በቁጥጥር ስር  ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተጣርቶ በእስራት እንዲቀጡ እየተደረገ ነው ። በጦር መሳሪያ ታግዘው ከባድ ወንጀል የፈጸሙና በአስገድዶ መድፈር መሳተፋቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸው አራት ግለሰቦች ከ8 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል ። በተመሳሳይ ሁኔታ ከጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ቀላልና ከባድ ወንጀል የተሳተፉ 26 ሰዎች ከ5 ወር እስከ 7 ዓመት የሚደርስ የእስራት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። "ከ70 በላይ ተጠርጣሪዎች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸው እየታየ ነው" ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ምናሉ በተለያዩ ወረዳዎች ከ60 በላይ ተጠርጣሪዎች በመኖራቸው ለህግ የማቅረብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል ። ወንጀለኞችን ለህግ  አሳልፎ በመስጠት በኩል ህብረተሰቡ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ጠቁመው፣ በአሁኑ  ወቅት የአካባቢው ሰላም ወደ ቀድሞው መረጋጋት  መመለሱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም