በጉዲፈቻ የሄዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህጻናትና ወጣቶች የትውልድ አገራቸውን እንዲጎበኙ እየተደረገ ነው

68
ኢዜአ ነሀሴ 3/2011 ወደ ተለያዩ ዓለም አገራት በጉዲፈቻ የሄዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህጻናትና ወጣቶች የትውልድ አገራቸውን እንዲጎበኙ እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ "በጉዲፈቻ  ወደ ጣልያን የሄዱ 40 ኢትዮጵያውያን ባለፈው ሳምንት የትውልድ አገራቸውን ለመጎብኘት አዲስ አበባ ገብተዋል"። እንዲሁም በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ  የሄዱ 77 ልጆች በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት ከአሳዳጊ ወላጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንም አብራርተዋል። በዚህም  በአክሱም፣ ላሊበላና አርባ ምንጭ ከተሞች የሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ  የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ መደረጉንም ተናግረዋል። በዚህም ወጣቶቹ የትውልድ አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲያውቁና ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ማጠናከር እንዲችሉ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል። ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በቀጣይም በአገሪቷ በሚከናወኑ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ በቀጣይም ወደ ሌሎች አገራት በጉዲፈቻ የሄዱ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው በማምጣት የትውልድ አገራቸውን እንዲጎበኙ የማድረግ ስራ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም