በኢንዱስትሪ ፓርኮች 90 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

73
ነሐሴ 2 ቀን 2011 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተቋቋሙ አንስቶ ለ90 ሺህ ዜጎች ጊዚያዊና ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ከእነዚህም ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ስራቸውን ለቀዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ መክሯል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፓርኮቹ  በአገሪቷ ለስራ እድል ፈጠራ፣ የወጪ ንግድን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ነው የተቋቋሙት። በስራ እድል ፈጠራም 50 ሺህ ቋሚ የስራ ዕድል ሲፈጠሩ 40 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ጊዚያዊ የስራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል። ፓርኮቹ ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ሰፊ  የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና የታለማላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው የተባለው። አሁን ባለው የመሰረተ ልማት አቅርቦት  ተዛማጅ ጉዳዮች ሳቢያ ወደ ስራ የገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚጠበቅባቸው ልክ የስራ ዕድል እየፈጠሩና የሚጠበቅባቸው ዓላማ እያሳኩ አለመሆኑም ተጠቁሟል። በተለይ በመብራት፣ በውሃ፣ በመንገድና በመኖሪያ ቤት አቅርቦት ሳቢያ በርካታ ሰራተኞች  ስራቸውን ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸው ነው የተነገረው። እስካሁንም ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች ስራቸውን የለቀቁ ሲሆን በርካታ የሰው ሃይል የለቀቀው በሀዋሳና በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆኑ ተነግሯል። በተጨማሪም ግንባታቸው የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው በመሰረተ ልማት አለመሟላት እንደሆነም ተጠቁሟል። ወደ ስራ ለገቡት ፓርኮችም ከተጠየቀው 306 ሜጋዋትሃይል  ውስጥየቀረበውከግማሽበታችመሆኑተጠቁሟል። ለዚህም እንደ ችግር የሚነሳው የተቋማት ተናቦ አለመስራትና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ስራ በእቅድ ውሰጥ አካቶ በጋራ ያለመስራት ነው ተብለዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች  የኤክስፖርት አቅማቸውን ለማሳደግና የስራ ዕድል ፈጠራን በበቂ ሁኔታ ለማሳካት የመሰረተ ልማት አቅርቦታቸው በተገቢው ሁኔታ ማሟላት ተገቢ መሆኑም በመድረኩ ተነስቷል። ለዚህም ስኬት ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና  በትኩረት መስራት እንደለባቸውም እንዲሁ። የኢንዱሰትሪ ፓርኮች ከተቋቋሙ ካለፉት አምስት ዓመታ ት ጀምሮ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ211 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ይታወቃል። በአገሪቱ ከ12 በላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገነቡ ሲሆን አምስቱ ወደ ስራ ገብተዋል፤ አራቱ ደግሞ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም