በአዲስ አበባ አዲስ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ ጀመረ

120
አዲስ አበባ ኢዜአ 2/2011 ለግንባታው ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ሜላዥያ ኮፊ ሮስተር የተባለ የቡና ማቀናባበሪያ ፋብሪካ ስራ ጀመረ። የሜላዥያ ኮፊ ሮስተር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ካሳ በምርቃው ወቅት እንዳሉት ፤ባለቸው አቅም ለአገራቸውና ህዝባቸው የድርሻቸውን ለማበርከት ኢንቨስት ማድርጋቸውን ገልጸዋል። ፋብሪካው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና ተፈላጊ የሆነውን የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ያደርጋል። ለውጭ ገበያ ከሚያቀርበው ምርትም ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ ፋብሪካው  አሁን ላይ ስራውን የጀመረው ከ40 ሰራተኖችን በመቅጠር ሲሆን በቀጣይ በሚደረግለት ማስፋፊያ ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥራል። ፋብሪካው አተር በርን የተባለ አዲስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት በመሆኑ ከአየር ብክለት ነፃ መሆኑንም አስረድተዋል። ፋብሪካው በሰዓት 720 ኪሎ ግራም ቡና ቆልቶ የሚያዘጋጅ ሲሆን በተመሳሳይ የተለያየ መጠን ያላቸው 1 ሺህ 800 ከረጢት የተቆላና የተፈጨ ቡና ያሽጋል። ፋብሪካው የቡና ምርትን እሴት ጨምሮ የሚያቀርብ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም