በአማራ ክልል የቅርስ ሀብትን በማልማትና በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

57
ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ነሀሴ 2 ቀን 2011- በአማራ ክልል ያለውን ሰፊ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቅርስ ሀብት በማልማትና በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ያለፈው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም የሚገመግምበትና የ2012 በጀት ዓመት ዕቅዱን የሚያስተዋውቅበት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል። የቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛት አብዬ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በዚህም ከ11 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አገራዊና የውጭ ጎብኚዎችን በማስተናገድ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በማግኘት የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። “በቱሪዝም ዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በተሰራው ስራም 13 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል። አቶ ግዛት እንዳሉት የአማራ ክልል ካለው ሰፊ የቱሪዝም ሃብት አንጻር በርካታ የሰው ኃይል በዘርፉ እንዲሰማራ በተሰራው ስራ ከ11 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ እድል ተፈጥሯል። “በቀጣይም በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በማስቆም፣ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመለየትና በማልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ጥራትን ቀልጣፋነት በማሻሻልና ለመሰረተ ልማት ትኩረት በመስጠት ከዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት በቱሪዝም ልማትና በቅርስ እንክብካቤ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ አድርጓል። ቢሯቸው በክልሉ 17 ሚሊዮን ብር በመመደብ ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶችን ለመጠገን እንዲውል ማድረጉንም አመልክተዋል። እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ በዓመቱ የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች ፌስቲቫል እንዲሁም የሰባት ቤት አገው የፈረስ ጉግስንና በክልል የሚገኙ ወረዳዎች የሚሳተፉበት የባህላዊ እሴቶች ትርኢት በክልል ደረጃ ተከብረዋል። እነዚህ የማይዳሰሱ ባህላዊ እሴቶች ነባር ክዋኔያቸውን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ተጨማሪ ቱሪስትን ለመሳብ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሞ ታረቀኝ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ሻደይ የልጃ ገረዶች ጨዋታን ጨምሮ ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ቅርሶች አሉ። “ቅርሶቹን በመለየት፣ በጥናት በማስደገፍና በማስተዋወቅ በተለይም የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት ካለው ሃብት ጋር ሲነጻጸር አናሳ ነው” ብለዋል። በቀጣይም ዞናቸው ከክልልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ቱሪዝምን አንዱና ዋናው የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግና በእዚህም ወጣቱን ትውልድ በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ቢሮው ማካሄድ የጀመረው የአፈጻጸም ግምገማና የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እንደሚቀጥል ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም