በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጁ

56
ነቀምቴ (ኢዜአ) ነሀሴ 1 ቀን 2011 - በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ መሀመድ አባሚልክ እንድተናገሩት በበጀት ዓመቱ በዞኑ በግንባታ ላይ ከነበሩት 11 የመስኖ ፕሮጀክቶች አምስቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል። የተጠናቀቁት አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ከ20 ሚሊዮን 270 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን 315 ሄክታር መሬት ማልማት ያስችላሉ። “በመስኖ ፕሮጀክቶቹ ከ780 በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉም” ተናግረዋል። ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ያሉ ቀሪዎቹ የመስኖ ፕሮጀክቶች ከ326 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸውና ከ1 ሺህ 187 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል። በግንባታ ላይ ያሉት ፕሮክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። እንደኃላፊው ገለጻ በተያዘው አዲሱ በጀት ዓመት 7 ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ከ37 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት ታቅዷል። የመስኖ ፕሮጀክቶቹ 264 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሲሆን ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቀም አመልክተዋል። በዞኑ የጅማ ራሬ ወረዳ የኢብሳ ኢላሙ ቀበሌ አርሶ አደር ተሾመ ወርቁ በሰጡት አስተያየት ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአካባቢያቸው መገንባታቸው በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ  በማልማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ ሲያለሙ ከፍተኛ ጉልበት ያወጡ እንደነበር ገልጸው አሁን በዘመናዊ አሰራር ሲጠቀሙ ጉልበታቸውን በመቆጠብ የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። “ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክት በአካባቢያቸው መገንባቱ በአካባቢው የብዙ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመለወጥ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ያሉት ሌላው የወረዳው አርሶ አደረ እራሱ ደርጩ ናቸው። በአቅራቢያቸው የሌላ ወረዳ አርሶ አደሮች በዘመናዊ የመስኖ ልማት ሥራ መሳተፍ ከጀመሩ ወዲህ በኑሮአቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውንም ገልጸዋል። ከእነሱ በመማር በቀጣይ በዘመናዊ የመስኖ ልማት ሥራ በመሳተፍ ሕይወታቸውን ለመቀየር ጠንክረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ በአንደኛና በሁለተኛ ዙር ከ44 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ በማልማት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዘገበው ኢዜአ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም