በናይሮቢ የኢፌዲሪ ኤምባሲ 64 ዜጎችን ወደ አገር ቤት መለሰ

60
ነሀሴ 1/2011 በናይሮቢ የኢፌዲሪ ኤምባሲ አስፈላጊ የጉዞ ሰነድ ሳይዙ ድንበር አቋርጠው በኬኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሉ ተይዘው ታስረው የነበሩ 64 ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው መለሰ። ተመላሾቹ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለው ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በኬንያ በኩል አቆራርጠው ሲሄዱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው። በመሆኑም ኤምባሲው ባደረገው ጥረት ባለፈው ሳምንት ናይሮቢ በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የነበሩና በኬንያ የፖሊስ ኃይል በቁጥጥር ስር ውለው ካዮሌ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ 54 ግለሰቦችን አስፈትቷል። በተመሳሳይ መልኩ ሞያሌ አካባቢ ድንበር ሲያቋርጡ የተያዙ 10 ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ 64 ግለሰቦችን ከኬንያ መንግስት ጋር ባደረገው ድርድር ክሳቸው ተቋርጦ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል። አምስት የሚደርሱ ደግሞ ከህገወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ስላቆያቸው በኤምባሲው የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። በኬንያ የኢፌዲሪ ኤምባሲ በተወከለባቸው አገራት ኬኒያን ጨምሮ (ኮሞሮስ፣ ማላዊ እና ሲሼልስ) የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወገኖቻችንን መብት ለማስከበርና ክብራቸውን ለማስጠበቅ ከአገሪቱ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች ጋር ተባብሮ እየሰራ ይገኛል። ይህንን ወገንን የመታደግ የዜጋ ዲፕሎማሲ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኢምባሲው በላከው መግለጫ አስታውቋል። በግንቦት 2011 ዓ.ም.ኤምባሲው 500 ያህል ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለሱ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም