የቅንጨ አረም በሰብላቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ

58
አክሱም  ነሀሴ 01 / 2011 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ተከስቶ እየተስፋፋ የመጣው የቅንጨ አረም በሰብላቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የዞኑ አርሶ አደሮች ተናገሩ። የግብርና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጧቸውም አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል። በዞኑ በታሕታይ ማይጨው ወረዳ ዱራ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር መኮንን ተክሉ እንዳሉት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱን እያሰፋ የመጣው የቅንጨ አረም ማሳቸውን ሙሉ በሙሉ እየወረረ መጥቷል። የአረሙ ፍሬ በቀላሉ በእንስሳት፣ በንፋሰ እና በውሃ ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀስ በእርሻ ማሳና በእንስሳት ግጦሽ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመስፋፋት ጉዳት እያስከተለ መሆኑን አስረድተዋል። “አረሙ በነቀላም ሆነ ጸረ አረም ኬሚካል በመርጨት አይጠፋም” ያሉት አርሶ አደር መኮንን፣ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተፈለገ በግብርና ምርታቸው ላይ የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የሚመለከተው የመንግስት አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በወረዳው የመዶገ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃነ ሰቋር በበኩላቸው፣ አረሙ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአክሱም ከተማ መብቀል እንደጀመረና ከጊዜ ወደጊዜ በቀበሌያቸው ጭምር እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል። “በሁሉም ማሳዬ ላይ አረሙ ተስፋፍቶ በሰብል ምርት ላይ ጉዳት እያደረሰብኝ ነው” ሲሉም መፍትሄ እንዲሰጣቸው። የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው የጠየቁት አርሶ አደሩ፣ በተናጠል በሚደረግ ጥረት አረሙ ማጥፋት እንደማይቻል ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። “የቅንጨ አረም በአሁኑ ወቅት ለአርሶ አደሩ አስቸጋሪ ሆኗል” ያለው ወጣት አርሶ አደር ጋይም ካሕሳይ ነው። እንደ ወጣቱ ገለጻ የቅንጨ አረም በአጭር ጊዜ በመስፋፋቱ ከዚህ በፊት ሲለማ የነበረው የእርሻ ማሳ በዚህ ክረምት ሳይለማ ቀርቷል። አረሙን የተመገቡ እንስሳት የወተት ምርታቸው እንደሚቀንስ በተጨባጭ ማረጋገጣቸውንም ጠቁመዋል። የዞኑ የእጽዋት ክሊኒክና የተባይ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ ረዳኢ በላይ በበኩላቸው እንዳሉት የቅንጨ አረም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ተስፋፍቶ ይገኛል። “በከተሞችና በየመንገዱ ዳር በብዛት ይታይ የነበረው የቅንጨ አረም በአሁኑ ወቅት በሚታረስና በማይታረስ መሬት ላይ ጭምር እየተስፋፋ ነው” ብለዋል። እስካሁን በተደረገው ጥናትም በዞኑ ውስጥ 1 ሺህ ሄክታር መሬት በአረሙ መሸፈኑን አቶ ረዳኢ ገልጸዋል። ይህ አረም የበቀለበት ማሳ ምርት እንደማይሰጥ መረጋገጡና በእንስሳ እና በሰው ላይም የጤና ችግር እንደሚፈጥር አመልክተዋል። “አረሙ እንዳይስፋፋ ከበቀለ በኋላ ሳያብብና ፍሬ ሳያፈራ በመንቀል በእሳት ማቃጠል ያስፈልጋል” ያሉት ባለሙያው፣ ከተቃጠለ በኋላ ጉድጓድ ውስጥ በመሰብሰብ ለኮምፖስ አገልግሎት ማዋል እንደሚቻል አስረድተዋል። አርሶ አደሮቹ በማሳቸው የበቀለውን የቅንጨ አረም ነቅለው ወደ ወንዝ እና በእንስሳት የግጦሽ መሬት ላይ መጣላቸው ለአረሙ መስፋፋት ምክንያት መሆኑንም አቶ ረዳኢ አስረድተዋል። የዞኑ መስተዳድር የእርሻና ገጠር ልማት አስተባባሪና የኢኮኖሚ ጉዳይ አማካሪ አቶ ተክለጊዮርጊስ አሰፋ በበኩላቸው “የቅንጨ አረምን በዘመቻ ለማጥፋት እቅድ፣ የመተግበሪያ መርሀግብርና አቅጣጫ ተይዞለት እስከ ወረዳ ድረስ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ብለዋል። ከክልል በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች ህብረተሰቡን በማነቃቃት አረሙን የማጥፋት ዘመቻ እስከ ነሀሴ ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚካሄድም አመልከተዋል። የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ህብረተሰቡን ከወዲሁ የማነሳሳት እና የማነቃቃት ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ ተክለጊዮርጊስ አመልክተዋል። የዞኑ አስተዳዳር ለችግሩ ተገቢ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸው፣ በዘመቻው ሁሉም አርሶ አደሮች እና የከተማ ማህበረሰብ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። የቅንጨ አረም በ1977 ዓ.ም ወደኢትዮጵያ እንደገባና በ1987 ዓ.ም ወደትግራይ ክልል ገብቶ መስፋፋቱ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም