የኢትዮጵያና የሱዳን የደህንነት ተቋማት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

59
ነሀሴ 1/2011 የሁለቱ አገሮች የደህንነት ተቋማት ሽብርተኝነትን፤ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ፣የገንዘብና የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የአገሮቹ የደህንነት ተቋማት የተደራጁ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር መስማማታቸውም ተገልጿል። በብሄራዊ ደህንነታቸው ዙሪያ በጋራ ለመስራት ባወጡት እቅድ መሠረት ከትላንት በስቲያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የሱዳን ኢንተሊጀንስ ሰርቪስ የጋራ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ታውቋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የሁለቱ አገሮች የደህንነት ተቋማት ሽብርተኝነትን፤  ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ፣ የገንዘብና የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ከኢትዮጵያ ስምምነቱን የፈረሙት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤልና የሱዳን ጄኔራል ኢንተሊጀንስ ሰርቪስ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል አቡበከር ዳምብ ላብ ናቸው። በሁለቱ አገሮች በድንበር ወሰን አካባቢዎች የሚፈጸሙ የተደራጁ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ተከታታይ ውይይቶችንና የመረጃ ልውውጦችን ያደርጋሉ። ኢትዮጰያና ሱዳን በድንበር ወሰን አካባቢዎች የሚፈጠሩ የተለያዩ የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል ከሁለቱ አገሮች የጸጥታና ደህንነት ኃላፊዎች ያሉበት ኮሚቴና በአገራቱ ድንበር የሚዋሰኑ ክልሎችን ያሳተፈ ቴክኒካል ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል። በቅርቡ ጥናት ላይ በመመስረት ሌሎች የጸጥታ አካላትን በማሳተፍ በተጠቀሱት ወንጀሎች ላይ ተከታታይ የኦፕሬሽን ስራ ለማካሄድ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም