የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ከጀትሮ- ጃፓን ድርጅት ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

60
ነሀሴ 1/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በጀትሮ የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ሊቀመንበር ሚስተር ኖቡሂኮ ሳሳኪ የተመራ ልዑካን ትናንት በጽህፈት ቤታቸውተቀብለው አነጋግረዋል። ዶክተር ማርቆስ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ጃፓን የቆየና መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው። የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደረሰን መግለጫ ያሳያል። የኢትዮጵያ መንግስት በጃፓን በሚካሄደው 7ኛው በቶክዮ-አፍሪካ የልማት ፈንድ ወይም ቲካድ (TICAD) ኮንፈረንስ የኢትዮጵያ ምርቶች ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉም ዶክተር ማርቆስ ገልጸዋል፡፡ የልኡካን ቡድን መሪ ሚስተር ኖቡሂኮ ሳሳኪ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ በማድነቅ፤ የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንስ መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል። አገሪቷ የጀመረችውን የኢንዳስትሪያላይዜሽን ጉዞ በመደገፍና ያለውን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የጃፓን ባለሃብቶች በስፋት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለባለሃብቶች እያደረገ ላለው ድጋፍም ሚስተር ኖቡሂኮ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያና ጃፓን ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም