በእነ ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ ለቀረበው መዝገብ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገ

66
ባህር ዳር ኢዜአ )ሐምሌ 29 / 2011-በባህር ዳር ከተማ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ለተጠረጠሩትና በእነ ብርጋዴል ጀኔራል ተፈራ ማሞ ለቀረበው መዝገብ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው። ፍርድ ቤቱ መረጃን በማደራጀት የክስ መመስረቻ የ15 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ለነሐሴ 13 ቀን 2011 እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ ፖሊስ ማስረጃዎችን ለማጠናከር ይችል ዘንድ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለዛሬ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል። በተሰጠው ጊዜ ውስጥም ፖሊስ 28 ምስክሮችን ማዳመጥ መቻሉንና ሌሎች አዳዲስ ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደቻለም ለችሎቱ አስታውቋል። ይሁን እንጂ አሁንም ሌሎች አዳዲስ የሰው ምስክሮችን፣ የፎረንሲክ ማስረጃዎችንና የኢትዮ-ቴሌኮም የስልክ ልውውጦችን ከፌደራል ለማስመጣት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ፖሊስ ችሎቱን ጠይቋል። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ በተጠሰው ጊዜ ውስጥ ማስረጃዎችን እያሰባሰበ ቢሆንም አዳዲስ በሚያዙ ተጠርጣሪዎች ደምበኞቻቸው ላይ መጉላላት እየተፈጠረ በመሆኑ ተለይቶ ሊቀርብ እንደሚገባ ተናግረዋል። በደንበኞቻችን ላይም ምስክር እየቀረበ ባለመሆኑ ገና በመፈለግ ላይ ባሉ መስካሪዎች ደንበኞቻችን መጉላላት የለባቸውም ሲሉም አቅርበዋል። ከኢትዮ ቴሌኮም እና  ከፎረንሲክ  ምርመራ የሚገኙ መረጃዎች ደህንነታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ደንበኞቻችን ሰነዱን የሚያገኙበትም ሆነ ሊቀይሩት የሚችሉበት አጋጣሚ ባለመኖሩ የጊዜ ቀጠሮ ምክንያት ሊሆን አይገባም ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በመርህ ደረጃ ተጠርጣሪ ሊያዝ የሚችለው ተጨባጭ ማስረጃ ተይዞ ቢሆንም እነዚህ ተጠርጣሪዎች የተያዙት ማስረጃ ሳይሰበሰብ በመሆኑ መጉላላት እየተፈጠረባቸው ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎች በልዩ ሁኔታ ተይዘዋል ቢባል እንኳ የሚሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ግልጽ ሊሆን ይገባል፤ ዋና ክስ ተመስርቶም ጎን ለጎን ማስረጃ ማሰባሰብ ስለሚቻል የጊዜ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም ሲሉም ተከራክረዋል። የሁለቱን ወገኖች ክርክር ያዳመጠው ችሎቱም ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን ማስረጃዎች መሰብሰብ እንዳለበት በችሎቱ አመልክቷል። “በመሆኑም የቀረበውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ አላምንበትም፤ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ክስ መመስረት ይገባዋል” በማለት ለጊዜ ቀጠሮ ሳይሆን የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ሰነዱን ለአቃቤ ህግ በማስረከብ ክስ መመስረት እንደሚገባውና ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፍተኛና በሰው መግደል በመሆኑ በማረሚያ ቤት እንዲቃዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በዚሁ ወንጀል የተጠረጠሩና በሌላ ችሎት ጉዳያቸው እየታየ ላሉ ተጠርጣሪዎችም በተመሳሳይ ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡም ትዕዛዝ መሰጠቱ ተመልክቷል። በእነ ብርጋዴል ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ 218 ተጠርጣሪዎች ተይዘው የነበረ ሲሆን ቀደም ሲል የማጣራት ሥራ ተከናውኖ 160ቹ መለቀቃቸው ይታወሳል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም