የኢትዮጵያን የቡና ምርት መለያ (ብራንድ) በዓለም ላይ ማስተዋወቅ ሊጀመር ነው

181
አዲሰ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 29/2011የኢትዮጵያን የቡና የምርት መለያ (ብራንድ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ከመስከረም 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። የኢትዮጵያን የቡና ምርት ብራንድ በሚመለከት ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያሰናዳው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል። የብራንድ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ምንሊክ ሀብቱ እንዳሉት ከአሁን በፊት የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ላይ የሚያስተዋወቅ አንድ መልክ ወይም ገጽ የለም። የሐረር፣ ሲዳሞና ይርጋጨፌ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቢሆንም እንደ ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን ቡና የሚያስተዋውቅ አገራዊ የቡና የምርት መለያ አለመኖሩ ችግር እንደፈጠረም አንስተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የቡና አውደ ርዕይና ጉባኤዎች ላይ ዋና የቡና ምርት መለያ ባለመኖሩ አንድ አይነት ገጽታ እንደሌለና ከዚህም አኳያ ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት ብልጫ እንደሚወሰድባት ጠቅሰዋል። ከኢትዮጵያ የቡና ምርት ጥራት ያነሰ ያላቸው አገራት ብራንዳቸውን አጉልተው በማስተዋወቅ በተሻለ ዋጋ ቡናቸውን እየሸጡ መሆኑንም ገልጸዋል። ሌሎች አገራት የሚያዘጋጇቸው የምርት መለያዎች በሰው አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋና የማይረሳ እንደሆነ ገልጸው ከዚህም አኳያ የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክ ተጠቅማ የቡና ብራንድ ሊኖራት ይገባል ብለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያን የቡና ምርት የሚያስተዋወቅ መለያ በማስፈለጉ ከአንድ ዓመት በላይ በወሰደ ጊዜ ብራንድ እንደተዘጋጀ ነው አቶ ምንሊክ ያስረዱት። ብራንዱን በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት፣ በዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤትና በሌሎች አገራት የማስመዝገብ ስራ በቀጣይ እንደሚከናወን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ለማስመዝገብ የሶስት ወር ጊዜ ስለሚፈጅ ሂደቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሚጀመርም ጠቅሰዋል። እንደ አቶ ምንሊክ ገለፃ ብራንዱን ከማስመዝገብ ጎን ለጎን በጃፓን ርዕሰ መዲና ቶኪዮ ከመስከረም 1 እስከ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የልዩ ጣዕም ቡና አውደ ርዕይና ጉባኤ ላይ በይፋ ማስተዋወቅ ይጀመራል። በቀጣይም በሌሎች የዓለም አገራት የማስተዋወቅ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የሲምፕሊ ብላክ አድቨርታይዚንግና ኮንሰልቲንግ ዋና ስራ አስኪያጅና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብበር ኤጀንሲ ተወካይ አቶ ዳዊት ለማ ብራንዱ በኢትዮጵያ ያለውን የቡና ታሪካዊ አመጣጥን ተከትሎ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል። ከክርስቶስ ልደት በፊት 10ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ግዛቶች መካከል በከፋ ካሊድ የሚባል የፍየል እረኛ ከሚጠብቃቸው ፍየሎች መካከል አንደኛዋ የሆነ የዛፍ ፍሬን ውይም ቅጠልን በልታ እንደ መዝለልና መጨፈር አይነት ባህርይ እንዳሳየች በታሪክ ይጠቀሳል። ካሊድዲ የዛን ዛፍ ቅጠል ወይም ፍሬ ቤቱ ወስዶ ሲቆላው ደስ የሚልና ልዩ ስሜት የሚሰጥ ሽታ እንደሸተተውና ከዛም በኋላ ቡናን በተለያየ መልክ መጠቀም መጀመሩ ይነገራል። የምርት መለያው ካሊድን፣ ፍየሉንና ቅጠሉን ወይም ፍሬውን እንደያዘና መለያው ቡናን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በከፍተኛ ሁኔታ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳም ገልጸዋል። ብራንዱን የማስተዋወቅ ሃላፊነት የሁሉም ዜጋ እንደሆነና የምርት መለያውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ጥራት ያለው ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑንና ጥራት ያለው ቡና መላክ የምርት መለያውን ደረጃ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የቡና ምርት መለያው መዘጋጀቱ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳት ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ቡና የሚወክል የምርት መለያ መዘጋጀቱን ቡናን በማስተዋወቅ እያሽቆለቆለ የመጣውን የኤክስፖርት ቡና ምርት ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ብራንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡ ሌሎች አገራትና ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ቡና የራሳቸው ምርት አድርገው እንዳይጠቀሙ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። ብራንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡት የሐረር፣ሲዳሞና ይርጋጨፌ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክት በጋራ እንደሚተዋወቁም አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም