በምስራቅ ጎጃም 304 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም ታርሶ በዘር እየተሸፈነ ነው

76
ደብረ ማርቆስ ሰኔ5/ 2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት  304 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም ታርሶ  እየተሸፈነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደተናገሩት በዘመኑ  ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ እንዲጠቀምበት በአማራጭነት የጀመሩት የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ነው፡፡ በዚህም ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የቢራ ገብስ፣ ጤፍ፣ ማሽላና ቦለቄ እንደሚለማ አመልክተው  እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቆሎና ማሽላ ዘር መሸፈኑን ገልጸዋል። በተደራጀ አግባብ የተግባር ስልጠና የወሰዱ ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ከሚገኙት ውስጥ ስምንት ሺህ ያህሉ ሴቶች እንደሆኑ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ " በኩታ ገጠም ከሚለማው መሬት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው፤ ከዚህ ውስጥም ሁለት ሚሊዮን ኩንታሉ ለፋብሪካዎች በቀጥታ የሚቀርብ ይሆናል" ብለዋል። ባለሙያው እንዳሉት የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ  አርሶ አደሮችን በተደራጀ አግባብ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የአረም፣ የተባይ መከላከልና የምርት ስብሰባውን በተመሳሳይ ወቅት ለማድረግ የጎላ ጠቀሜታ አለው። በኩታ ገጠም እያለሙ ካሉት አርሶ አደሮች መካከል በባሶሊበን ወረዳ የኮርክ ከበሌ ነዋሪ አቶ ደመቀ አንተሁነኝ በሰጡት አስተያየት  ባለፈው ዓመት በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ  ስንዴ በማልማት 80 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል። ይህም ከልማዳዊ አስተራረስ  ስንዴ በሄክታር  ከ20 ኩንታል በላይ ምርት ጭማሬ እንዳለው ጠቁመው፤ዘንድሮም ያላቸውን መሬት በተመሳሳይ ለማልማት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል። ዘንድሮ በኩታገጠም ለማልማት የራሳቸውን አንድ ሄክታር እና በኪራይ ያገኙትን ግማሽ ሄክታር ማሳ ጨምረው ስንዴ ለመዝራት  ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት ደግሞ በደብረኤሊያስወረዳ የጓይ ቀበሌ  አርሶአደር አለበል ተጋረድ ናቸው፡፡ አርሶአደሩ ባለፈው ዓመት በኩታ ገጠም የተሳተፉ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን በማየት እሳቸውም በተመሳሳይ ስራ ለመጠቀም መነሳሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በምስራቅ ጎጃም በ2010/2011 የምርት ዘመን በአጠቃላይ ከሚለማው 648 ሺህ ሄክታር መሬት ከ23 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም