በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የድንች ዝርያዎች እንዲቀርቡላቸው አርሶ አደሮች ጠየቁ

82
ባህር ዳር (ኢዜአ) ሐምሌ 28 / 2011- በሽታን ተቋቁመው ፈጥነው በመድረስ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ሁለት የድንች ዝርያዎች በብዛት እንዲቀርቡላቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን የቋሪት ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ። የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በፈንደቃ ጨጎዴ ቀበሌ በአምስት ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ በቅድመ ማስፋት ያባዛውን “በለጠ” እና “ጉደኔ” የተሰኙ የድንች ዝርያዎችን ትላንት በአርሶ አደሮች የመስክ በዓል አስጎብኝቷል። የፈንደቃ ጨጎዴ ቀበሌ አርሶ አደር መሰለ ኮከብ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል “ጉደኔ” የተባለ ምርጥ የድንች ዘር ሰጧቸው በሩብ ሄክታር መሬት አባዝተው 42 ኩንታል ዘር ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል። “ካገኘሁት ዘር 40 ኩንታሉን ለምርምር ማዕከሉ በማስረከብ ከዚህ በፊት የማላውቀውን 50 ሺህ 400 ብር ገቢ እንዳገኝ አስችሎኛል” ብለዋል። ዘንድሮም ያንኑ መሬት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም በማረስና የሚያስፈልገውን ግብዓት ጨምረው በማልማት እስከ 60 ኩንታል የድንች ዘር በማግኘት የተሻለ ገቢ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ኮነ ፍስሃ በበኩላቸው “ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት አርሶ አደሮች የተሞከሩ ሁለት አዲስ የድንች ዝርያዎች በሽታን በመቋቋምና ፈጥነው በመድረስ ከፍተኛ ምርት በመስጠት ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠናል” ብለዋል። “ነባር የድንች ዝርያዎች በበሽታ እየተጠቁና የሚሰጡት ምርትም በየጊዜው እየቀነሰ በመምጣቱ ስጋት ውስጥ ገብተን ነበር” ያሉት ቄስ ኮነ  በአዲሶቹ የድንች ዝርያዎች ተስፋቸው መመለሱን ተናግረዋል። “የአካባቢው መሬት የአፈር ለምነት እየተሟጠጠ በመምጣቱ በምርምር ማዕከሉ ቀርበው የተሞከሩ የድንች ዝርያዎች የምግብ ዋስትና ችግራችንን በዘላቂነት የሚያረጋግጡ በመሆኑ ዘሩ በብዛት ሊቀርብልን ይገባል” ሲሉም ጠይቀዋል። የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላዬ ተክለወልድ በበኩላቸው ለድንች ምርታማነት በክልሉ የድንች ዘር ብዜት ዕጥረት ዋነኛው ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል። “ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በኢንስቲትዩቱ ቲሹ ካልቸር ከበሽታ ንጹህ የሆኑ የድንች ዝርያዎችን በሳይንሳዊ ዘዴ አውጥቶ በማባዛት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል። በክልሉ በደቡብ ጎንደር፣ በአዊና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች በተመረጡ ደጋማ ወረዳዎች ያልተማከለ የዘር ስርዓትን ለመፍጠር የምርምር ማዕከሉ በአርሶ አደሮች ማሳ ንፁህ የድንች ዘር የማባዛት ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በምርምር ብቻ የድንች ዘር አቅርቦት የሚፈታ ባለመሆኑ የተደራጁ የድንች ዘር አባዥ አርሶ አደሮችን በመፍጠር፣ የግልና የመንግስት ዘር አባዥ ድርጅቶች ወደዚህ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የድንች ዘር አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት እንደሚሰራም አመልክተዋል ዶክተር ጥላዬ አንዳሉት በአርሶ አደር ማሳ በለጠ 281 ኩንታል፣ ጉደኔ 210 ኩንታል ምርት በሄክታር በአማካኝ የሚሰጡ በመሆኑ እነዚህን በማስፋትና አዳዲስ ዝርያዎችንም በምርምር በማውጣት የዘር አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ 300 ሺህ ሄክታር መሬት በድንች ሰብል እንደሚለማ የተናገሩት ደግሞ በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የድንች ተመራማሪና የብሔራዊ ድንች ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አለሙ ወርቁ ናቸው። “መሬቱን በምርጥ ዘር ለመሸፈን ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የድንች ዘር ቢያስፈልግም እስካሁን በምርጥ ዘር እየለማ ያለው መሬት ከሶስት በመቶ አይበልጥም” ብለዋል። የመንግስትም ሆነ የግል ዘር አባዥ ድርጅቶች እንደሌሎች የሰብል ዝርያዎች የድንች ዘርን ስለማያባዙ ዕጥረቱን ለመቅረፍ ማዕከሉ ከምርምር ስራው በተጓዳኝ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ዘር እንዲያባዙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ምስክር በበኩላቸው “በምርምር የሚወጡ የድንች ዝርያዎችን በሁሉም የክልሉ ደጋማ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ቢሮው በትኩረት ይሰራል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም