በቴክሳስ ኤል ፓሶ ከተማ የገበያ ማእከል አቅራቢያ 20 ሰዎች ተገደሉ

61
ኢዜአ ሀምሌ 28/2011 በቴክሳሷ  ከተማ ኤልፓሶ  በጅምላ  ተኩስ  20  ሰዎች ሲገደሉ 26 መቁሰላቸውን  ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የከተማዋ ገዢ ግሪግ አቦት ሁኔታውን “በቴክሳስ ታሪክ አጅግ የተጎዳንበት ቀን” ብለውታል፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመው ሲኤሎ ቪስታ ሞል አቅራቢያ የሚገኝ የገበያ ማእከል እቃ ማከማቻ ቦታ ላይ ሲሆን ከአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ጥቂት ማይሎች ብቻ እንደሚርቅም ታውቋል፡፡ በግድያው የተጠረጠረው  የ21 አመት ወጣት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ነዋሪነቱም በዳላስ አቅራቢያ የምትገኘው የአለን ከተማ ነዋሪ እንደሆነ ተገልጿል፣ አለን ከኤል ፓሶ 1ሺህ 46 ኪሎሜትር እርቀት ላይ እንድምትገኝም ዘገባው አመላክቷል፡፡ የአሜሪካን ሚዲያዎች ተጠርጣሪውን ፓትሪክ ክሩሰስ ተብሎ እንደሚጠራ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድርጊቱን “የፈሪና የጨካኞች ተግባር” ሲሉ አውግዘውታል፡፡ “የዛሬውን የጥላቻ ድርጊት ከሃገሬ ዜጎች ጎን ሆኜ አወግዛለሁ፣ ንፁሃን ዜጎችን መግደል በምንም መልኩ በምክንያትም ሆነ በይቅርታ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል በቲውተር ባስተላለፉት መልእክት፡፡ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች እስካሁን በስም ያልታወቁ ሲሆን በአንፃሩ የሚክሲኮው ፕሬዝዳንት ማኑኤል ሎፔዝ ኦፕራዶር ከሟቾች ሶስቱ ሜክሲኳውያን መሆናቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ የአሁኑ ጥቃት በካሊፎርንያ የምግብ ፌስቲቫል ላይ በታዳጊ ታጣቂ የተፈፀመውንና  ለሶስት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት  ሳምንት ሳይሞላው የተፈፀመ እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡ የቴክሳሱ ጥቃት በዘመናዊዋ አሜሪካ ለስምንተኛ ጊዜ የተፈፀመ የጅምላ ተኩስ እንደሆነ ዘገባው ገልጿል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም