በጋምቤላ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ማህበረሰባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸው ገለጹ

73
ሀምሌ 27/2011 በጋምቤላ ክልል ወጣቶች በክረምት የእረፍት ጊዜያቸው በተለያዩ  የበጎ ፍቃድ አገልገሎትና የልማት ስራዎች ላይ በመሰማራት የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ለማገዝ መዘጋጀታቸውን ገለጹ ። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በከተማው በተለያዩ ማህበራት ከተደራጁ ወጣቶች ጋር በመቀናጀት በጋምቤላ ከተማ የጽዳት ዘማቻ አካሄደዋል። ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዓለሙ ጥሩነህ በሰጠው አስተያየት በክረምቱ የእረፍት ጊዜው በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች በመሰማራት የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማገዝ መዘጋጀቱን ተናግሯል። በተለይም በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ልማትና ጥበቃ ስራዎች መሰማራት እንደሚፈልግ ገልጿል። ከአሁን በፊትም ቢሆን የክረምት የእረፍት ጊዜው አቅመ ደካሞችን ለማገዝ የፈረሱባቸውን ቤቶቻቸውን  በመጠገን  ጊዜውን ያሳልፍ እንደነበር የተናገረው ደግሞ ሌላው ተመራቂ ብስራት የሸዋስ ነው። ብሰራት እንዳለው በተየዘው የክረምት ወቅትም ም ተመሳሳይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ከከተማው ወጣቶች ጋር በመቀናጀት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ማካሄዳቸውንና ይህም በከተማው ለነበራቸው ቆይታ ማስታወሻ  እንዲሆናቸው ገልጿል ። በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የበጎ ፍቃድ አስተባበሪ መምህር ፈለቀ ተረፈ  ከተመራቂ ተማሪዎች ጋር በመሆን በከተማው የተለያዩ  የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማከናውን ቢያቅዱም በጊዜ መጣበብ ምክንያት የተወሰኑት መፈጸም እንዳልቻሉ ተናገረዋል። ሆኖም  ተመራቂ ተማሪዎች በዕለቱ ያካሄዱትን የጽዳት ፣ የችግኝ ተከላና የተተከሉትን በመንከባበከብ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አመልክቷል። በማህበር ከተደራጁ የከተማው ወጣቶች መካከል ወጣት መንግስቱ ለላጎ በሰጠው አስተያየት በተያዘው  ክረምት ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመቀናጀት የተዘጉ ቱቦዎችን በማጽዳት ፣ ችግኝ በመትከልና አቅመ ደካሞችን ለማገዝ በመዘጋጀት  ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግሯል። በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  የጽዳት ዘመቻን ጨምሮ በአምስት የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ማቀዳቸውን  የገለጸው ደግሞ የወገን ደራሽ ወገን ማህበር ተጠሪ ወጣት አሳዬ ተረፋ ነው። ከሚሰማሩባቸው መካከል ወላጆቻቸውን ላጡ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብና የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት ይገኙበታል። የጋምቤላ ክልል ሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አጁሉ ኡቻር እንደገለፁት በክልሉ በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 20 ሺህ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ። ወጣቶቹ በሚሰጡት አገልግሎት 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም