ለውጡን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየሰራ ነው

71
አዳማ /ኢዜአ/ ሐምሌ 27/201 ሀገሪቱ የጀመረችውን የማህበራዊና ምጣኔ ሀብት ሪፎርም ስራዎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን የኦሮሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበር ገለፀ። ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል። በኮንፈረንሱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበር ፕሬዚዳንት   ፕሮፌሰር ግርማ ገብረሰንበት እንደገለጹት ማህበሩ የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ከመሰረቱ ለመለወጥ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳካት ሀገር በቀል ዕውቀትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አቀናጅቶ ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰ ነው። በምርምር የተገኙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችና አዳዲስ አሰራሮችን ለክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች  ለማዳረስና የሀገሪቱን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብት ሪፎርም ተግባራትን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ዘላቂ ልማትና ዕድገት በሀገሪቱ  እንዲኖር በግብርና፣በኢነርጂ ፣በቴክኖሎጂ ፣ በጤና፣ በትምህርት፣በተፈጥሮ ሀብትና በሌሎችም የልማት ዘርፎች  የተካሄዱ 38 የጥናት ውጤቶች በኮንፈረንሱ እንደሚቀርቡ  ፕሮፌሰር ግርማ ተናግረዋል። የኮንፈረንሱ ዓላማ የጥናት ውጤቶቹን በሃሳብ በማዳበር ለመንግስትና ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ማድረስ በሚቻልበት ሂደት ላይ በክልሉና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር በመምከር የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው። ማህበሩ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አሜሪካና ካናዳን ጨምሮ ከአውሮፓ፣ አውስትራሊያ ፣ህንድና ሌሎች በቴክኖሎጅ ከበለፀጉ የእሲያ ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል። ምስረታውን በሲዊዲን ሀገር ያደረገው የኦሮሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበር በሀገሪቷ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ህዝቡን በዕውቀት ለማገልገል ወደ ሀገር ቤት መግባቱንም አስረድተዋል። "በአምቦና በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲተሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል እንዲቋቋም በማድረግ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እያከናወንን እንገኛለን "ያሉት ፕሮፈሰር ግርማ በራሳቸው የልህቀት ማዕከል ያደራጁት ዩኒቨርሲቲዎችንም በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ማህበሩ በተጨማሪም የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ቋንቋ ለማሳደግ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የራሱ የሆነ የልህቀት ማዕከል በማደራጀት በስምንት የጥናትና የምርምር ዘርፎች ላይ  እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። "በተለይም በውሃ ሀብት፣በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ፣በህዋ ሳይንስ፣በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ልማት ፣በአካባቢ ጥበቃና መሰረተ ልማት  ላይ  የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን "ብለዋል። የኦሮሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበር በውጭው ዓለም ያለውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣አዳዲስ አሰራሮችንና ልምዶችን ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ የሚያደርገውን ጥረት ዩኒቨርሲቲው ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ዶክተር ለሚ አስታውቀዋል። የኦሮሞን ህዝብ ቋንቋና ባህል ለማሳደግ ማህበሩ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም አመልክተዋል። በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣በአርሲ ዩኒቨርሲቲዎችና በኦሮሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበር ትብብር በተዘጋጀው ኮንፈረንስ በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የኦሮሞ ምሁራንና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም