የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ለሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ችግሮች ተጋልጠዋል- ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን

96
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ሐይቆች በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ችግር እየገጠማቸው መሆኑን የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ካንቹላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተፋሰሱ የሚገኙ በርካታ ሐይቆች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ብክለት እየደረሰባቸውና የውሃ መጠናቸውም እየቀነሰ ነው። ለአብነትም ለሰው መጠጥና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውለው ዝዋይ ሀይቅ አራት ሄክታር የሚሆነው ክፍሉ በእንቦጭ አረም መወረሩን ተናግረዋል። የሐይቁ ገባር የነበሩ ሶስት ወንዞች መጠለፋቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ "ሐይቁ መጠኑ እየቀነሰ በመምጣቱ በአካባቢው ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና ፋብሪካዎች የወደፊት ስጋት ነው" ብለዋል። አካባቢው በጣም የተራቆተ በመሆኑ በዝናብ ወቅት አፈር እየተሸረሸረ ወደ ሐይቁ በመግባት የደለል ክምችት አስከትሏል ያሉት ዋና ዳይሬከተሩ፤ የውሃ መጠኑ እንዲቀንስ በማድረግ ችግሩን ማባባሱን አስረድተዋል። አብጃታና ሻላ ሐይቆች በየዓመቱ ከአምስት መቶ ያላነሱ የአዕዋፍ ዝርያዎች ከአውሮፓ ተሰደው ሐይቆች ላይ እንደሚያርፉ ጠቁመው፤ እነዚህም ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሀብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። አብጃታና ሻላ ሐይቅ የውሃ ምንጩ ከዝዋይ ሐይቅ የሚነሱ ሁለት ወንዞች መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ከበደ፤ ዝዋይ አደጋ ውስጥ ከገባ ለአብጃታ ሐይቅም ስጋት መሆኑን ነው የተናገሩት። የተፋሰሱ አብዛኛው ሐይቆች ጨዋማና ለእንቦጭ አረም የማይመቹ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደፊት ግን አረሙ በሌሎች ሐይቆች ላይ ላለመከሰቱ ዋስትና እንደሌለም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ተፋሰሱ ካለው መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ በመሆኑ ሐይቆቹን ለብክለት የሚዳርጉ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል። ተፋሰስ ባለስልጣኑ ችግሩን በጊዜያዊነትና ዘላቂነት ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። ለአብነትም በዝዋይ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን አረም የአካባቢውን ሕብረተሰብ በማስተባበር በጊዜያዊነት አረሙን የማስወገድ ስራ እየተከናወነ እንደሆነ አንስተዋል። የእንቦጭ አረም በአባያ ሐይቅ ላይ መከሰቱን አውስተው፤ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ጋር የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ሐይቁ የባሕር እንስሳት ያሉበት በመሆኑ በሰው ጉልበት ለመከላከል ከባድ እንደሆነ ገልጸው፤ በአካባቢው ከሚገኘው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሙያና ቴክኒክ ባለሙያዎች የማስወገጃ ማሽን መሰራቱንና ወደፊትም ወደስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል በሁሉም ሐይቆች የሚገኝባቸው በደን ጭፍጨፋና አካባቢ መራቆት የደረሰባቸው ወረዳዎች ጋር በመሆን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። "በዚህ ዓመትም የተለያዩ የአፈር ጥበቃ እርከኖች ተሰርተዋል፤  ከ30 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል፤ 65 ሺህ ሄክታር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ተደርጓል" ብለዋል። "የተለያዩ የውሃ ማቆያ ዘዴዎችን ሰርተናል፤ ቦረቦር መሬቶችን ወደ ሳርነት የመቀየር ስራዎችን እየሰራ ነው" በማለትም አክለዋል።። በውሃ ሀብት ሁሉም የመጠቀም መብት ቢኖረውም ሀብቱ የሚጎዳ በመሆኑ ውሃ የበከለንና የተጠቀመ አካል በውሃ ሀብት አስተዳድር ፖሊሲ መሰረት የሚከፍልበት አሰራር ለመዘርጋት ጥናት መደረጉን አውስተዋል። የሐይቆች የውሃ መጠን እየቀነሰ መሆኑን ተከትሎ ለእርሻና ለእንስሳት ንክኪ የበለጠ ችግር እያስከተለ በመሆኑ፤ "በሐይቆች ዳርቻ ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ክልል እንዲኖር እየሰራን ነው" ብለዋል። በተፋሰሱ ሐይቆች በርካታ ኢንዱስትሪዎች፣ የእንስሳት እርባታዎችና ቄራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ሐይቆችንና የሐይቆችን ሥነ ምህዳር ከብክለት ለመጠበቅ መንግስት፣ ግለሰቦችና አጋር አካላት ያሉበት አደረጃጀት ተፈጥሮ የመከላከል ስራ አየተከናወነ እንደሆነ አመልክተዋል። በመንግሰት በጀት ሁሉንም ችግሮች መፍታት እንደማይቻል ገልጸው፤ የተለያዩ የግል ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሰራ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል። ሰባት ሐይቆችን ያቀፈው ተፋሰሱ፤ በአምስት ንዑሳን ተፋሰሶች የተዋቀረ ሲሆን፤ 53 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋትና 12 ሚሊዮን ነዋሪዎች እንዳሉት ይገመታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም