በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ አዋሳኝ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በእርቅ ተፈታ

96
ዲላ ሚያዝያ 25/2010 በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ዛሬ በተከናወነው በባህላዊ የእርቅ ስነስርዓት ተፈታ። እርቁ የተከናወነው  ለዞኖቹ አዋሳኝ በሆነው ኤዴራ በተባለ ቦታ በሁለቱም ህዝቦች በሚታወቀው ጎንዶሮ በተባለ ባህላዊ ስነስዓት ነው። የእርቅ ስነስርዓቱም ሁለቱም ህዝቦች አባገዳዎች አማካኝነት ነው የተካሄደው። የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ ጂሎ ማኖ በእርቁ ስነስርዓት  ወቅት " ጌዴኦና ጉጂ ከጥንት ጀምረው አንድ ሆነው የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው፤ በመካከላቸው ምንም ዓይነት ፀብ የሚያስነሳ ነገር የለም፤ በጎንዶሮ እርቅ ተመልሰን አንድ ሆነናል" ብለዋል። የጌዴኦ ብሄር አባገዳ ደንቢቦ ማሮ በበኩላቸው በባህላዊ መንገድ እርቀ ሰላም ከወረደ በኋላ የቀደመው ማህበራዊ ትስስር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። "የቀደመውን አንድነታችንን በማጠናከረም እጆቻቸውን ለልማትና  ለሰላም ብቻ ማንሳት ይኖርብናል" ሲሉም መክረዋል። በስነስርዓቱ ወቅት የሁለቱም ህዝቦች አባገዳዎች፣ የፀጥታ አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች መገኘታቸውን በስፍራው የተገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም