ኢትዮጵያ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ አይደለችም- የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች

61
አዲስ  አበባ  ሐምሌ 27/2011 ኢትዮጵያ አሁን ላይ ቀጣዩን ብሄራዊ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ እንደማትገኝ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ። ኢትዮጵያ የ2012 ብሄራዊ ምርጫን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ እንደማትገኝና ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ በመስጠት መስራት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ። የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮቹ በህጉና በህገ መንግስቱ መሰረት ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ቢካሄድ ፍላጎታቸው ቢሆንም አሁን ከምርጫ ይልቅ በትኩረት መሰራት ያለበት በሰላም ጉዳይ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህ ደግሞ ገዥውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለብሄራዊ ምርጫው መሳካት የድርሻቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል። እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ የአገሪቷ ሰላም ሳይረጋገጥ ''ምርጫ ካልተደረገ ሞቼ እገኛለሁ'' ማለት አላዋቂነት ነው። መራጩ ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጀንዳ ጠንቅቆ ባልተረዳበት ሁኔታ ምርጫን ማካሄድ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት መሆኑንም ያነሱ አሉ። የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዑመር መሃመድ ምርጫ ያለሰላምና መረጋጋት የማይታሰብ ነው ይላሉ። ይሁንና አሁን አገሪቷ ያጋጠማትን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈታ በማድረግ የ2012 ምርጫን ማካሄድ አለባት ብለዋል። ለምርጫው በጣት የሚቆጠሩ ወራት የቀሩ ቢሆንም መንግስትና ባለድርሻ አካላት የሰላም ችግሩን በመፍታት ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲከናወን ጥረት ማድረግ አለባቸውም ነው ያሉት።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም