የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች በ3ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ ዘር እያባዙ ነው

59
ፍቼ ሐምሌ 27/ 2ዐ11 የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ ዘር እያባዙ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ የግብርና ቴክኖሎጂ ብዜት ማስፋፊያ ኃላፊ ወይዘሮ በሃብቷ አበራ ዛሬ እንደገለጹት ዝርያው የሚባዛው በነባር ገብስ አብቃይነታቸው በሚታወቁት ግራር ጃርሶ፣ ደገም፣ ያያ ጉለሌ ፣ጅዳና ደራ ወረዳዎች ነው። በወረዳዎቹ በሚገኙ 78 ቀበሌዎች እየተከናወነ ባለው የዘር ብዢ ከ7ሺ 6ዐዐ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል። በዚህም ከ4ዐ ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። አርሶ አደሮቹ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ዘር ለማምረት የሚያስችላቸውን ስልጠና ከማግኘታቸው ሌላ በልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል። አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ምርጥ ዘር ከወቅቱ ገበያ በ2ዐዐ ብር ብልጫ ባለው ዋጋ በማስረከብ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውን ስምምነት በአካባቢያቸው ከሚገኙ ዩኒየኖችና የኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር ማድረጋቸውንም አመልክተዋል። ከአርሶ አደሮቹ የሚሰበሰበውን ምርጥ ዘር በመጠቀም በዞኑ ሰባት ወረዳዎች በሚገኙ 121 ቀበሌዎች ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንዳለ በጥናት መረጋገጡንም ኃላፊዋ ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቢራ ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ ያሟላ የቢራ ገብስ ማምረት እንደሚቻል በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል 800 በሚሆኑ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ባካሄዱት ሙከራ ማረጋገጡን አስረድተዋል ። አርሶ አደሮቹ ከዚህ በተጨማሪ ሽንብራ፣ምስርና አተር ዘርበማምረት በገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ወይዘሮ በሀብቷ ገልጸዋል ። አርሶ አደሮቹ ከሩብ ሄክታር እሰከ አንድ ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን ለሙከራና ለሰርቶ ማሳያ በመስጠት መተባበራቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል። በገበያ አዋጭ የሆነውን የገብስ ምርጥ ዘር በማምረትና በማባዛት ተጠቃሚ ለመሆን በለፉት ሶስት ዓመታት ማሳቸው ላይ ከምርምር ተቋማት ጋር መስራታቸውን የተናገሩት የግራር ጃርሶ የቶርባን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ፉላሳ ነገዎ ናቸው። በዚህም ምርታማ የሚያደርገኝን ትምህርትና ልምድ ቀስሜበታለሁ ብለዋል። ምርጥ ዘር የአርሶ አደሩ የማሳ ክትትልና ድጋፍ ከተደረገ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት ለማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል ። ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ጆቴ መርጊያ በዘር ማባዛት ሙከራ በመሳተፍ ልምድእንደቀሰሙና ይህንንም ለሌሎች ለማስተላለፍ እንደሚጥሩ ተናግረዋል። አሁን በአንድ ሄክታር መሬት ላይያለሙትንየገብስ ዘርበማባዛት ተጠቃሚ ለመሆንም የክብካቤና ድጋፍ ሥራዎችን ከልማት ጣቢያ ሠራተኞች ጋር እያከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በዞኑ በድንች ፣በሽንብራ፣ በገብስና ስንዴምርጥ ዘር ለማባዛትና ለማስፋፋት በምርምር ተቋማት የተደገፈ ጥናት  እየተደረገ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም