አገሪቱ በሁሉም መስክ ለጀመረችው የለውጥ እርምጃ ስኬታማነት እንሰራለን - የኦሮሚያ ክልል ምክትል ኘሬዝዳንት

55
አዳማ ሰኔ 5/2010 አገሪቱ በሁሉም መስክ ለጀመረችው የለውጥ እርምጃ ስኬታማነት እየተወሰዱ ያሉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ገልጠዋል። “የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያስተላለፈውን የፖሊቲካና የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኦህዴድና የክልሉ መንግስት በሙሉ አቅማቸው ይሰራሉ'' ብለዋል። “ስራ አስፈፃሚው በሀገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማስቀጠል፣ በምስራቅ አፍሪካ አሰተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢና ወቅቱ የሚጠይቀው ነው'' ብለዋል። የኢትዮ- ኤርትራ ችግር እልባት ለመስጠት ኮሚቴው የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ለቀጠናው ሰላምና ለህዝቦች አብሮ መኖር እንዲሁም  ለጋራ ተጠቃሚነት  ፋይዳው የላቀ መሆኑን ምክትል  ፕሬዝዳንቷ ገልጠዋል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለማቃለል የኢህአዴግ ሰራ አስፈፃሚ ያስለፈው ውሳኔ ተገቢ መሆኑን  ጠቅሰው የግል ባለሀብቱ በመንግስት የልማት ድርጅቶች በከፊልም  ሆነ ሙሉ በሙሉ የአክሲዮን ድርሻ እንኖረው ለተወሰነው ውሳኔ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ህብረተሰቡም ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መጠናከር ከመሪ ድርጅቱና ከመንግስት ጎን  በመሆን እንዲረባረቡ ሚክትል ፕሬዝዳንቷ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም