ዩኒቨርስቲው የትራፊክ ደህንነትና የመንገድ ዳር መብራቶች ችግር ለመፍታት ድጋፍ እንደሚሰጥ ገለጸ

74
ሶዶ ኢዜአ ሐምሌ 26/2011  የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በከተማው የትራፊክ ደህንነት መጠበቂያና የመንገድ ዳር መብራቶች ችግር ለመፍታት ድጋፍ አንደሚሰጥ ገለጸ። የዩኒቨረሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ እንደገለፁት ተቋሙ በአካባቢው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል። የወላይታ ሶዶ ከተማ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያደገ በመምጣቱ የነዋሪው ህዝብ ቁጥርም ሆነ የተሽከርካሪዎች ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ይህንኑ ተከትሎ አስደንጋጭ የትራፊክ አደጋ የሚደርስበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመው "ጨለማን ተገን በማድረግ የመንገድ ዳር መብራት በሌለበት አካባቢ የወንጀል ምልክቶች ይታያሉ" ብለዋል ። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የትራፊክ ፖሊሶችንና የመንግስት የደህንት ስራዎችን ለማገዝ በአራት ዋና ዋና ቦታዎች የትራፊክ ደህንነት መጠበቂያ መብራቶች እንደሚተከሉ  አስረድተዋል ። ለጨለማ ተጋላጭነታቸውን በጥናት በተለዩ ቦታዎች አስር ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን የመንገድ ዳር የመብራት  መስመር እንደሚዘረጋ ፕሮፌሰር ታከለ ገልጸዋል። በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ለሚከናወኑ እነዚህ ስራዎች ዩኒቨርሲቲው 11 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንም አስታውቀዋል። የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ሻንካ በበኩላቸው በከተማው የሚፈጠሩ ሰው ሠራሽ አደጋዎች በነዋሪው ላይ ስጋት ፈጥረው መቆየታቸውን ገልፀው በዘላቂነት ለመፍታት የዩኒቨርሲቲው  እገዛ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል ። "በተለይ የመንገድ ዳር መብራት የሚቆምባቸው መንደሮች ፣የትምህርትና መሰል ተቋማት ያሉበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም