ሊቢያ ሶስት የስደተኛ ማቆያ ማዕከላትን ልትዘጋ እንደሆነ ተገለፀ

85
ሀምሌ 26/2011 የሊቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፋቲ ባሻጋሃ ሊብያ ከግዙፎቹ የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ሶስቱን የመዝጋት ዕቅድ እንዳላት ይፋ አደረጉ ተባለ፡፡ እንደ ዘገባው  ለመዘጋት የታቀዱት በሚስራታ፤ በታጁራ እና በኮሆመስ የሚገኙ የስደተኞች ማዕከላት ናቸው። ይህ መግለጫ የተሰጠው በሐምሌ ወር የታጁራ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል በሚሳኤል ተመቶ  ከ20 የሚበልጡ ስደተኞች ከሞቱ በኋላ ስደተኞቹን ዳግም ወደ ቦታው የመመለስ ስራ ከፍተኛ ትችትን በማስተናገዱ እንደሆነ መረጃው አስፍሯል። የታጁራ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል የሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የትሪፖሊ መንግሥት እና  መሠረቱን  በቤንጋዚ ያደረገው  የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ኃይል ጦርነት በሚያካሄዱበት አቅራቢያ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል። በሊቢያ ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉ ድርጅቶች የማዕከሎቹ መዘጋት ሌሎች ማዕከላትን ከማጨናነቁ በተጨማሪ በርካታ ስደተኞች በህገ ወጥ ደላሎች እጅ የመውደቅ እድላቸው ቀላል ይሆናል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው እየገለፁ ይገኛሉ። ባለፈው ሳምንት ብቻ 150 ስደተኞች ሊቢያን ለቀው ወደ ጣሊያን ሲጓዙ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህም በዚህ አመት ብቻ በሜዲትራኒያን ባህር ህይወታቸውን ካጡ ስደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም