መንግስት ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ የማድረግ አቋሙ ጽኑ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

90
ሀምሌ 25/2011 የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ የማድረግ ጽኑ አቋም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ በህግ አግባብ እንደሚፈታም አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ መንግስት አሁንም የሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ  ጽኑ አቋሙ እንዳለው አመልክተዋል። ከዚህ ቀደም ይፈጸም እንደነበረው ጥፍር መንቀልና ጨለማ ቤት የማስቀመጥ ዓይነት ድርጊት እንደማይፈጸም አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የዴሞክራሲ አውድን የማስፋትና የማዘመን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ህግ የማስከበር ተግባር ቂም ከመበቀል ጋር ተነጣጥሎ መታየት እንዳለበትም ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ሰው ወንጀልን የመከላከል ተግባር ከራሱ መጀመር እንደሚገባው ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣትና በየዕለቱ አደናቃፊ ስራ በማከናወን ለውጡን የሚያደናቅፉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ እርምጃ ይወሰድ ቢባል በርካታ ሰዎች ወንጀለኛ ሆነው እንደሚገኙ ገልጸዋል። በሌላ በኩል የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ የቆየ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸው፤ ጥያቄው ፖለቲካዊ መብት እንደሆነ አመልክተዋል። አንድ ክልል እንደ አዲስ ክልል ሆኖ ሲቋቋም ቀደም ሲል አብሮ ከነበረው ክልል ጋር የተሳሰረባቸው ጉዳዮች መታሰብ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ''ሁሉም ህዝብ ብቻውን በመቆሙ ወይም ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በጋራ በመቆሙ የሚያገኘውን ትርፍና ያጋጥመውን ኪሳራ ከፖለቲካ ትርፍ ውጪ በዝርዝር ማየት ጠቃሚ ነው'' ብለዋል። ሲዳማ ክልል ሆኖ ቢወጣ በአካባቢው ያለ ችግር ሁሉ ይፈታል ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል። የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ የህዝቦች መሆኑን በድምጻቸው ካረጋገጡ ህግን ተከትሎ የሚፈጸም እንደሚሆን ተናግረዋል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም